ዶሮ በመስረቅ የሞት ፍት የተፈረደበት ናይጄሪያዊ ምህረት እንዲደረግለት ዘመቻ ተጀምሯል
ከ10 አመት በፊት ከፖሊስ መኖርያ ቤት ውስጥ እንቁላል እና ዶሮ በመስረቅ ክስ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ነበር
በናይጄሪያ ከ2012 ጀምሮ 3400 ሰዎች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ውሳኔው እስኪፈጸም እየተጠባበቁ ይገኛሉ
ሴጉን ኦሉዌኬሬ የተባለው ናይጄርያዊው የ17 አመት ታዳጊ ወጣት እ.ኤ.አ በ2010 ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን ወደ አንድ የፖሊስ አባል መኖርያ ቤት ያቀናሉ፡፡
ወጣቶቹ ስለት እና የእንጭት ሽጉጥ በመያዝ አስፈራርተው የተወሰኑ ዶሮዎች እና እንቁላሎችን ሰርቀው ይሰወራሉ፡፡
ከጥቂት ጊዚያት በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በ2014 በኦሱና ክልል በሚገኝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተላለፈባቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ በስቅላት ሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ ሁለቱ ወጣቶች ሌጎስ በሚገኝው ኪሪኪሪ በተባለ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት እስር ቤት ውስጥ ከሌሎች ሞት ፍርደኞች ጋር ውሳኔው እስኪፈጸም ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡
በወቅቱ ቅጣቱ ከጥፋቱ ጋር አልተመጣጠነም በሚል በመላው ናይጄሪያ ከፍተኛ ቁጣ በመቀስቀሱ ውሳኔው እስካሁን ሳይፈጸም ለአስር አመት ቆይቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም ቤተሰቦቹ ከሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ከእስር እንዲለቀቅ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኦሱን ክልል አስተዳዳሪ አዲሞላ አዲሊካ ወጣቱ ኦሉዌኬሬ እና ጓደኛው ጥፋተኛ በተባሉበት ክስ ከበቂ በላይ ቅጣት ተቀብለዋል። ነገር ግን የሞት ፍርድ ተመጣጣኝ ቅጣት አይደለም ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
አስተዳዳሪው በጉዳዩ ዙርያ ከክልሉ ፍትህ ኮሚሽነር ጋር መነጋገራቸውን እና በቅርቡ ፍትሀዊ የሆነ ውሳኔ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡
አስተዳዳሪው ይህን ካሉ በኃላ ጉዳዩ ዳግም በናይጄርያ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ አጀንዳ ሆኗል። የፍርድ ውሳኔው እንዲቀየርም ዘመቻ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በ17 አመቱ እስር ቤት ገብቶ አሁን ላይ የ31 አመት ወጣት የሆነው ሴጉን ኦሉዌኬሬ በ2025 መጀመርያ ላይ ከእስር ቤት እንደሚለቀቅ ይጠበቃል፡፡
ከ2012 ጀምሮ የሞት ቅጣት አስፈጽማ በማታውቀው ናይጄሪያ እስካሁን 3400 የሞት ፍርደኞች ቅጣታቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡