ለፋሲካ በዓል የተገዛው አውራ ዶሮ ጎረቤቶችን አላስተኛ ብሏል በሚል ክስ ተመስርቶበታል
የናይጀሪያ ፍርድ ቤት ለበዓል ማድመቂያ የተገዛው ዶሮ በአፋጣኝ እንዲታረድ መስኖበታል
የአውራ ዶሮው ባለቤት በበኩሉ ዶሮውን ከፋሲካ በዓል በፊት ማረድ አልችልም ሲል ተናግሯል
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ ለፋሲካ በዓል ማድመቂያ በሚል የተገዛው ዶሮ በሶስት ቀናት ውስጥ እንዲታረድ መወሰኑ ተገልጿል።
በሀገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት የሆነችው ካኖ ግዛት የሚኖር አንድ ግለሰብ ለፋሲካ በዓል ማድመቂያ በሚል ነበር አውራ ዶሮ የገዛው።
ለበዓሉ ቀደም ተብሎ የተገዛው ይህ ዶሮ በሚያወጣው ድምጽ የተማረሩ ጎረቤቶች ጉዳዩን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት አምርተዋል።
ፍርድ ቤቱም ከሁለት ጎረቤቶች የቀረበለትን የዶሮ ድምጽ ረብሻ ያስቁምልን ጥያቄ ከመረመረ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የሱፍ መሀመድ የጠባለው ጎረቤት ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዳስረዳው ከሆነ አዲስ የተገዛው ዶሮ በእንቅልፍ ሰዓት በሚያሰማው ድምጽ መተኛት አለመቻሉን ገልጿል ተብሏል።
የዶሮው ባለቤት የሆነው ኢስያጉ ሹቡ በበኩሉ ዶሮውን በቅርቡ ለፋሲካ በዓል ማድመቂያ እንደገዛው እና ረጅም ጊዜ እንደማይቆይ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ክስ አቅራቢዎች እና ፍርድ ቤቱም የፋሲካ በዓል እስኪደርስ እንዲታገሱት የጠየቀው የዶሮው ባለቤት ከበዓሉ በፊት ግን ዶሮውን ማረድ እንደማይችል ተናግሯል ተብሏል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ የሆኑት ማጅስትሬት ሃሊማ በበኩላቸው ዶሮውን እስከ ነገ አርብ ድረስ እንዲያርድ ፈቃድ የሰጡ ሲሆን ባለቤቱም ዶሮው ጎረቤቶቹን በድምጽ እንዳይረብሽ የሆነ መላ እንዲፈልግ አስጠንቅቀዋል።
ይሁንና በጎረቤቶቹ ክስ የቀረበበት አውራ ዶሮ ከአርብ በኋላ በህይወት ከቆየ እና ጎረቤቶቹን ከረበሸ ቅጣት እንደሚጣልበት ዳኛው ማስጠንቀቃቸው ተገልጿል።