ልዩልዩ
ናይጀሪያዊቷ እንስት በረጅም ዊግ የአለም ድንቃድንቅ መዝገብን ተቀላቅላለች
ሄለን ዊሊያምስ 351 ሜትር የሚረዝም ዊግ ከጸጉሯ ጋር በመስራት ነው ስሟን በአለማቀፉ መዝገብ ያሰፈረችው
የአለማችን ረጅሙን ዊግ ለመስራት 11 ቀናት እና 2 ሺህ 500 ዶላር ፈጅቷል
ናይጀሪያዊቷ ሄለን ዊሊያምስ የአለም ረጅሙን ዊግ በመስራት በድንቃድንቅ መዝገብ ስሟን ማስፈር ችላለች።
ሄለን 351 ነጥብ 28 ሜትር የሚረዝም ዊግ (ሰው ሰራሽ ጸጉር) ለመስራት 11 ቀናት ፈጅቶባታል።
የአለማችን ረጅሙ ዊግ 1 ሺህ ጥቅል ዊጎች እና 6 ሺ 250 ማስያዣዎች ጥቅም ላይ ውለዋል።
ረጅሙን ዊግ ሰርቶ ለመጨረስ በአጠቃላይ 2 ሚሊየን ናይራ ወይም 2 ሺህ 500 ዶላር ወጪ ማድረጓንም ነው ሄለን የተናገረችው።
ላለፉት ስምንት አመታት በጸጉር ስራ ላይ ብሰማራም ረጅሙን ዊግ ለመስራት ቀላል አልሆነልኝም የምትለው ሄለን ዊሊያምስ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሟን ማስፈር በመቻሏ ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች።
ረጅሙን ዊግ ሰርቶ አጠናቆ ለእይታ ማቅረብና ማስለካት ሌላኛው ፈተና ነበር።
እናም ሌጎስን ከአቤኩታ ከተማ በሚያገናኘው አውራ መንገድ ተዘርግቶ የአለም ድንቃድንቅ ባለሙያዎችም ለክተው እውቅና ሰጥተዋታል።
ሌላኛዋ ናይጀሪያዊት ሂልዳ ባቺ በዚሁ አመት ለረጅም ስአት ምግብ በማብሰል የአለም ክብረወሰንን መስበሯ ይታወሳል።
የሂልዳ ሪከርድ ግን ከሳምንታት በፊት በአየርላንዳዊው አለን ፊሸር መሰበሩ አይዘነጋም።