በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 አመራሮቹን ከአባልነትና ከፖለቲካዊ ሥራዎች አግጃሁ አለ
ከፓርቲው ተሰናብተዋል የተባሉ አባላት “ህገ ወጥ ገንዘብ በመበተን ፓርቲውን ለማፍረስ እየጣሩ ነው” በሚል ተኮንነዋል

ህውሓትን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የያዙትን ስልጣን ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ውሳኔ እንዲያገኝ ይደረጋል ብሏል
በደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው አዲሱ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 16 ከፍተኛ አመራሮቹን ከፓርቲው አባልነት እና ፖለቲካዊ ሥራዎች ማገዱን አስታወቀ።
ፓርቲው እነ አቶ ጌታቸው ረዳ "ይቅርታ ጠይቀው ወደ ፓርቲው እንዲቀላቀሉ የሰጠኋቸውን የአንድ ወር ጊዜ ሳይጠቀሙበት ወሩ በመጠናቀቁ ከፓርቲው አባልነትም ሆነ ሀላፊነት ተሰናብተዋል" ብሏል።
ከዚህ ባለፈም ፓርቲውን በመወከል በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የያዙትን ስልጣን ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ውሳኔ እንዲሰጠው ይደረጋል ሲል አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ህውሓት ባደረገው 14ኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ያልተሳተፉ የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮቹን በፓርቲው ውስጥ ካላቸው ኃላፊነት እንዳነሳ አስታውቆ ነበር፡፡
አዲስ የተቋቋመው ማዕከላዊ ኮሜቴ በሳምንቱ መጨረሻ ቀን አደረኩት ያለውን ስብሰባ ተከትሎ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች ዙርያ ባወጣው መግለጫ ከፓርቲው አባልነት የታገዱት ሰዎች “ከውስጥ ሆነው ድርጅቱን ለማፍረስ ከሚሠሩ አካላት ጋር በመመሳጠር እየሰሩ ችግር ሲፈጥሩ ነበር” የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በተጨማሪም “በፓርቲው ውክልና ያገኙትን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስልጣን በመጠቀም እና ህገወጥ የሆነ በርካታ ገንዘብ በመበተን በፓርቲው ውስጥ ሁነው ፓርቲውን ለማፍረስ እና የክልሉን ህዝብ አንድነት ለመበታተን እየሰሩ ነው” ሲል ኮንኗል።
በዚህም መግለጫው አቶ ጌታቸውን ረዳን ጨምሮ ከፓርቲ አባልነት ተሰናብተዋል የተባሉት 16ቱ ከፍተኛ የህውሓት አመራሮች ፓርቲውን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ውሳኔ የመወሰን መብት የላቸውም ብሏል።
ላለፉት 50 አመታት በላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዕከል ሆኖ የቆየው ህውሓት ከፌደራል መንግስቱ ጋር የገባበትን ጦርነት በስምምነት ካጠናቀቅ በኋላ ለምርጫ ቦርድ የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።
ሆኖም ምርጫ ቦርድ በቀደመው እና በድሮው አዋጅ የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ህጋዊ አሰራር የለም በሚል በልዩ ፓርቲነት እንደመዘገበው ማስታወቁ ይታወሳል።
ከፓርቲው ህጋዊ ሰውነት መመለስ እና ከስልጣን ፍላጎት ጋር በተያያዘ በደብረጽዩን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እና በአቶ ጌታቸው ረዳ መካከል ለሁለት የተከፈከለው ፓርቲው ባለፉት ወራት በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ፓርቲው ላካሄደው 14ተኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና ውሳኔዎች ምንም አይነት እውቅና እንደማይሰጥ አስታውቋል።