በጎንደር ከተማ እና ዙሪያው ምን አዲስ ነገር አለ?
ከትናንት ጀምሮ በጎንደር የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል አዲስ ውጊያ በማድረግ ላይ ናቸው
በአማራ ክልል የተጀመረው ጦርነት ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል
በጎንደር ከተማ እና ዙሪያው ምን አዲስ ነገር አለ?
በአማራ ክልል ካሉ ከተሞች አንዷ በሆነችው ጎንደር ከተማ እና ዙሪያዋ አደሲ ግጭት መቀስቀሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
እንደ ነዋሪዎች አስተያየት ትናንት መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ነው በከተማዋ የተኩስ ድምጽ የተሰማው፡፡
ሸዋ ዳቦ ወይም ቀበሌ 18 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተጀመረው ይህ የተኩስ ድምጽ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ተስፋፍቷል ተብሏል፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ ለአል ዐይን እንዳሉት “የተኩስ ድምጹ ትናንት አመሻሽ ላይ አልፎ አልፎ ይሰማ ነበር ዛሬ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ግን እየጨመረ መጥቷል” ብለዋል፡፡
የተኩስ ልውውጡ በማን እና ማን መካከል ነው? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ያው የተለመደው በመከላከያ-ልዩ ሀይል-ሚኒሻዎች እና ፋኖ መካከል ነው” ሲሉም ነግረውናል፡፡
የተኩስ ልውውጡ በቀላል እና ከባድ የጦር መሳሪያ የታገዘ መሆኑን የሚናገሩት እኝህ አስተያየት ሰጪ የሚተኮሰው መሳሪያ ድምጽ ከምሳ ሰዓት በኋላ መቀነስ አሳይቷል ብለዋል፡፡
ቀበሌ 03 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤት ላይ ከባድ ጦር መሳሪያ ማረፉን ተከትሎ ቤት ውስጥ የነበሩ ህጻናትን ጨምሮ የአንድ ቤተሰብ አባላት መጎዳታቸውን ሰምቻለሁ ሲሉም ተናግረዋል እኝህ አስተያየት ሰጪ፡፡
በተባባራሪ ጥይት ላለመታት የከተማዋ ነዋሪዎች በየቤታቸው እንዳሉ የተናገሩት እኝህ አስተያየት ሰጪ በተለይም በከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የትራንስፖርት እንቅስቀሴ መቆሙን፣ ባንኮችን ጨምሮ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው የአራዳ አካባቢ ነዋሪ በበኩላቸው ትናንት ምሽት ጀምሮ አንገርብ፣ ደፈጮ እና ሌሎች የከተማዋ መግቢያ እና መውጫ አካባቢዎች ላይ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ ነዋሪዎች በየቤታቸው እንደቆዩ ተናግረው “እኔ ባለሁበት አካባቢ ግን የተኩስ ልውውጥ አልሰማሁም፣ ትራንስፖርትም አልፎ አልፎ አለ፣ አምቡላንሶች ግን ለየት ባለ መንገድ በብዛት ሲመላለሱ አይቻለሁ” ሲሉ ነግረውናል፡፡
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተራዘሙ ግጭቶች ምክንያት የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰው ቀጥለዋል -ኢሰመኮ
በዛሬው ዕለት ከምሳ ሰዓት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ እየሰሙ እንዳልሆነ የተወሰኑ ተዘግተው የነበሩ የንግድ ቤቶች እየተከፈቱ መሆኑን እኝህ አስተያየት ሰጪ አክለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳድር እና የአማራ ክልል ጸጥታ ቢሮ ሃለፊዎች በጎንደር እና ሌሎች የክልሉ ቦታዎች ለይ እየተደረጉ ባሉ የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ ምላሻቸውን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችም መልሼ አደራጃለሁ ካለበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ይህንን ጦርነት ተከትሎ ክልሉ ለ10 ወራት ያህል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢቆይም አሁንም ክልሉ ወደ ቀድሞ የሰላም ሁኔታው ያልተመለሰ ሲሆን ኢንተርኔት አገልግሎትም ሙሉ ለሙሉ አልተለቀቀም፡፡
የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት በክልሉ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ለንጹሃን ዜጎች ሞት፣ ንብረት ውድመት እና የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈጸሙ በማድረጉ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቅሰዋል፡፡