ኢትዮጵያ በነዳጅ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለችውን እገዳ ታነሳ ይሆን?
100 ሺህ የኤሌክትሪክ መኪኖች ያሏት ኢትዮጵያ የጥገና እና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች አልተሟሉም
ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ ያገደች የመጀመሪያዋ ሀገር ተብላለች
ኢትዮጵያ በነዳጅ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለችውን እገዳ ታነሳ ይሆን?
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከስድስት ወራት በፊት በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መታገዱ ይታወሳል፡፡
የፈረንሳዩ ለሞንድ ጋዜጣ ይሄንን የመንግስት ውሳኔ አስመልክቶ በሰራው ዘገባ ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ ያገደች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች ብሏል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ኢትዮጵያ ውሳኔውን ያስተላለፈችው በየዓመቱ የምታወጣው ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወጪን ለመቀነስ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት 120 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ግማሹ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኙም የሚለው ይህ ዘገባ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማት አለመሟላቱንም ጠቅሷል፡፡
እንዲሁም ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ጥራት መቆጣጠሪያ መመሪያ የላትም ያለ ሲሆን ከ2025 በኋላ የጥራት ቁጥጥር ሊጀመር እንደሚችል ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ሰምቻለሁም ብሏል፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ላሉት የኤሌክትሪክ መኪኖች ጥገኛ መስጫ እና ቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማት እጥረት በስፋት ከመኖራቸው ባለፈ ጥራታቸው ያልተረጋገጡ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ወደ ገበያው እየገቡ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም ኢትዮጵያ እስከ 2026 ባሉት ዓመታት ውስጥ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧ የተገለጸ ሲሆን ድርጅቱ በፍትሀዊ የንግድ ውድድር የሚያምን በመሆኑ ይህ እገዳ እንዲነሳ ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚችልም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሁለት ወር በፊት ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዳያስገቡ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
እንዲሁም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እገዳ መተላለፉ በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ለይ አሉታዊ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል እና በልዩ ሁኔታ በተለይም በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች እንዲፈቀድላቸው መጠየቁ ይታወሳል፡፡