በህንድ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ100 ማለፉ ተገለጸ
በደቡባዊ ህንድ ኪራላ ክልል የደረሰውን አደጋ ተከትሎ 200 ወታደሮች በነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተዋል
በአደጋው የጠፉ ሰዎችን ለማፈላለግ የሚደረገውን ጥረት በአካባቢው እያጣለ የሚገኝው ከባድ ዝናብ አደጋች አድርጎታል
በደቡባዊ ህንድ ኪራላ ክልል ዋይንዳ በተባለ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 106 መድረሱ ተገለጸ፡፡
ተራራማ በሆነው አካባቢ ዛሬ ንጋቱን በጣለው ከባድ ምክንያት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የተጎዱ ሰዎችን ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት የቀጠለ ሲሆን በአካባቢው እየጣለ በሚገኝው ከባድ ዝናብ እና በአደጋው የድልድዮች መሰበር የፍለጋ ስራውን ፈታኝ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ቢቢሲ የአካባቢው ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ህይወታቸው ካለፉ ሰዎች በተጨማሪ 129 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ ወታደሮች በስፍራው የነፍስ አድን ስራው ላይ የተሰማሩ ሲሆን 250 ሰዎችን ከአደጋው በመታደግ ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ አዘዋውረዋል፡፡
ኪራላ የተባለው ክልል በ2018 ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ 400 ሰዎች መሞታቸው ሲታወስ የአሁኑ አደጋ ከ2018ቱ በመቀጠል አስከፊው ነው ተብሏል፡፡
አደጋው በደረሰበት አካባቢ እስከ 350 የሚደርሱ ቤተሰቦች እንደሚኖሩ የተገለጸ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የመሬት መንሸራተቱ ዋይንዳ ከተባለው ወረዳ በተጨማሪ በሌሎች አራት ወረዳዎችም ላይ የተከሰተ ሲሆን የሰዎች አስክሬን አደጋው ከተከሰተበት ስፍራ ራቅ ባሉ ወንዞችም ላይ መገኝቱ ነው የተሰማው፡፡
የመሬት መንሸራተቱ ሰዎችን መኖሪያ ቤቶችና እና ተሸከርካሪዎችን ሲወስድ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ እየተዘዋወረ ይገኛል፡፡
የአካባቢው ባለስልጣናት ለአደጋው ፈጣን ምላሽ በመስጠት የተረፉ ሰዎችን ማፈላለግ ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የድልድዮች መሰባበር በመሬት መንሸራተቱ ተውጠው የሚገኙ ሰዎችን በህይወት ለማትረፍ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንደሚያደርገው አስታውቀው በገመድ እና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም ወደ ስፍራው በቶሎ ለመድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአውሮፕላን የሚደረገው አሰሳ በስፍራው የሚጥለው ከባድ ዝናብ እስኪያባራ ድረስ ተቋርጧል። በተጨማሪም በአካባቢው ከሚገኙ 14 ኮሌጅ እና ትምህርት ቤቶች አስሩ እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡
የህንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ለእያንዳንዳቸው 200 ሺህ ሩፒ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡