ሰሜን ኮሪያ በ6 ወራት ውስጥ ያስወነጨፈችው የሚሳዔል መጠን 25 ደርሷል
ሰሜን ኮሪያ በአንድ ቀን ብቻ ስምንት የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ወደ ምስራቅ የባህር ክልሏ ማስንጨፏ ተገለፀ።
ሰሜን ኮሪያ የባላቲክ ሚሳዔል ሙከራውን ያደረገችው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በፊሊፒንስ ባር ላይ ስያካሂዱ የነበሩትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተነግሯል።
የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አዛዥ በሰጡት መግለጫ፤ ሰሜን ኮሪያ ሚሳዔሎቹን በዛሬው እለት ያስወነጨፈችው ከፒዮንግያንግ በስተሰሜን ከሚገኝ ሱናን ከተባለ ስፍራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሚሳዔሎቹ ከምድር ከ25 እስከ 90 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ከ110 እስከ 600 ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት መብረራቸውንም ገልፀዋል።
የጃፓን መንግስት በበኩሉ “ሰሜን ኮሪያ የባላስቲክ ሚሳዔል ነው ተብሎ የሚጠረጠር መሳሪያ አስወንጭፋለች” ሲል አስታውቋል።
ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት ያካሄደችው የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራ ጨምሮ የፈረንጆቹ 2022 ከገባ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ18ኛ ጊዜ ሲሆን፤ አጠቃላይ ያስወነጨፈችው ሚሳዔል መጠንም 25 መድረሱ ተገልጿል።
የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ ሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ፑንጌይሪ ከተማ አቅራቢያ የኒውክሌር ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች እንደሆነ ምልክቶች ታይዋል ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ በያዝነው ዓመት የተገመተውን የኒውክሌር ሙከራ ካካሄደች ከፈረንጆቹ 2006 ወዲህ ብቻ ለ7ኛ ጊዜ እንደሚሆንም ይጠበቃል።
ሰሜን ኮሪያ ከ10 ቀናት በፊት በአንድ ቀን ብቻ አንድ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔልን ጨምሮ ሶስት የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏ ይታወሳል።
ሰሜን ኮሪያ መጀመሪያ ላይ ያስወነጨፈችው አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳዔል መሆኑ የተገመተ ሲሆን፤ 540 ኪሎ ሜትር ገደማ የተጓዘ መሆኑ የደቡብ ኮቲያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ሁለተኛው ሚሳዔል ከመሬት በ20 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ በመብረር ላይ እያለ ከእይታ መሰወሩን ያስታወቀችው ደቡብ ኮሪያ፤ 3ኛ ሚሳዔል ደግሞ በ60 ኪሎ ሜትር ከፍታ 760 ኪሎ ሜትሮችን ያክል መጓዙ ተነግሯል።