ሰሜን ኮሪያ በምስራቅ ዩክሬን ለሚገኙት እና በሩሲያ ለሚደገፉት ተገንጣይ ግዛቶች እውቅና ሰጠች
ሩሲያ ሁለቱን ተገንጣይ ግዛቶች ነጻ ለማውጣት መወሰኗን ማስታወቋ ይታወሳል
ሰሜን ኮሪያ ለተገንጣይ ግዛቶቹ እውቅና በመስጠት ከሩሲያ እና ሶሪያ ቀጥሎ 3ኛ ሀገር ሆናለች
ሰሜን ኮሪያ በምስራቅ ዩክሬን ለሚገኙትና በሩሲያ ለሚደገፉት ሁለት ተገንጣይ ግዛቶች ነጻ ሀገር የሚል እውቅና መስጠቷን የሰሜን ኮሪያን ሚዲያ ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እርምጃው ለሁለቱ በሩሲያ ለሚደገፉ ተገንጣይ ግዛቶች ማለትም ለዶንቴስክን እና ለሉሃንስክ ግዛቶች የሀገርነት እውቅና በመስጠት ከሩሲያ እና ሶሪያ ቀጥሎ ሰሜን ኮሪያን 3ኛ ሀገር ያደርጋታል፡፡
የዶንቴስክ መሪ ዴኒስ ፑሺሊን በቴሌግራም ቻናሉ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ፍሬያማ ትብብር” እና ከ4,000 ማይል (6,500 ኪሎ ሜትር) ርቀት ላይ ከምትገኘው ኒውክሌርየር ከታጠቀች ከሰሜን ኮሪያ ጋር የንግድ ልውውጥን እንደሚያሳድግ ተስፋ አድርገዋል።
በሞስኮ የሚገኘው የዶንቴስክ ኤምባሲ በቴሌግራም ቻናል ላይ በለጠፉት ፎቶ በሞስኮ የሰሜን ኮሪያ አምባሳደር ሲን ሆንግ ቾል የዶንቴስክ ተወካይ የእውቅና ሰርተፊኬት ሲሰጡ ታይተዋል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዠን እንደዘገበው ከሆነ የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሁለቱ ግዛቶች የነጻ ሀገርነት እውቅና ደብዳቤ መላካቸውን ዘግቧል፡፡ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በደብዳቤው የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት ለማዳበር እንደሚሰሩ መናገራቸውም ተጠቅሷል፡፡
ሩሲያ ሁለቱን ተገንጣይ ግዛቶች ነጻ ለማውጣት መወሰኗን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ የኔቶ ጦር ወደ ቀድሞ የሶቬት ሀገራት መስፋፋት ለደህንነቷ እንደማያሰጋት በመግለጽ ነበር በዩክሬን ላይ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ያወጀችው።ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬንን ትጥቅ ማስፈታት እና የናዚን አስተሳሰብ ማጥፋት የዘመቻው አላማ መሆኑን ሩሲያ መግለጿ ይታወሳል።
በሩሲያ ርምጃ የተቆጡት ምእራባውያን ሩሲያን ያዳክማል ያሉትን ሁሉ ማእቀብ በሩሲያ ላይ ጥለዋል።ጦርነቱ አሁንም በደቡብ እና ምሰራቃዊ ዩክሬን ቀጥሏል።