የሰሜኑ የሀገሪቱ ጦርነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ምን አይነት ጫና እያሳደረ ነው?
30 በመቶ የኢትዮጵያ ክልሎች ጦርነት ላይ ናቸው፤ ይህም ሀገሪቱ ወደማንችለው ጉዳት እወሰዳት ነው- አቶ አማን ይሁን ረዳ
የመንግስት በጀት የጦርነት ወጪዎችን ለመሸፈን እየዋለ መሆኑ ጦርነቱ ያልተካሄደባቸውን ክልሎች ሳይቀር ይጎዳል ብለዋል
በትግራይ ክልል የነበረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ልዩ ሀይል መጠቃቱን ተከትሎ ነበር ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት የገባችው።
ይህ ጦርነት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ ቢጀመርም እስከ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ተካሂዶ የአገር መከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱ ይታወሳል።
መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ የትግራይ ህዝብ ያልተቆራረጠ የሰብዓዊ ድጋፎችን እንዲያገኝ እና አርሶ አደሮች ወደ ክረምት የግብርና ስራ እንዲመለሱ በሚል ከትግራይ ለመውጣቱ በምክንያትነት ስቀምጧል።
ይሁንና አሁን ላይ ጦርነቱ ከተግራይ በተጨማሪ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተዛምቶ እድሜው ለጦርነት የደረሰ እና የጦር መሳሪያ ያላቸው ዜጎች ወደ ጦርነት እንዲገቡ በርካታ ክልሎች የክተት አዋጆችን በማሰማት ላይ ናቸው።
አል ዐይን አማርኛ ይህ በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ወዴት ያመራል? ምንስ አይነት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል? ሲል የፖለቲካ-ኦኮኖሚ ምሁራንን ጠይቋል።
አቶ አማንይሁን ረዳ በሙያቸው የንግድ አማካሪ ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያም ተሳታፊ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት አሁን ላይ 30 በመቶ የኢትዮጵያ ክልሎች ጦርነት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ጦርነቱ ሰብአዊ ጉዳቱ እንዳለ ሆኖ ልንወጣው ወደማንችለው ጉዳት እየወሰደን ነው ብለዋል።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጦርነት የሚሸከም አይደለም የሚሉት አቶ አማን ይሁን በዓለማችን ላይ ከተካሄዱ ጦርነቶች በስምምነት ያልተፈታ ጦርነት ባለመኖሩ ወደጦርነት የገቡ አካላት ወደ ስምምነት እንዲመጡ አሳስበዋል።
በጦርነቱ ለምነን እና ተበድረን የገነባናቸውን መሰረተ ልማቶች እያሳጣን ነው፤ ጦርነቱ በመቀጠሉ ምክንያት ተጨማሪ ጉዳት ላለማስተናገዱ ምንም ዋሰትና የለንም እና ስምምነት የግድ መሆን አለበት ብለዋል።
“ወቅቱ የግብርና ስራዎች የሚከናወንበት ዋነኛው የእርሻ ስራ ነው፤ ለስራ ዝግጁ የሆነ እና ማምረት የሚችል ወጣት ደግሞ ወደ ጦርነት እየተመመ መሆኑ ዜጎቻችንን ከማሳጣት አልፎ በኢትዮጵያ የምርት እጥረት እንዲፈጠር እንደሚያደርግም” አቶ አማንይሁን ተናግረዋል።
“ወትሮም ቢሆን በብዙ ምክንያቶች እየተፈተነ ያለው ኢኮኖሚያችን ወደተራዘመ ጦርነት መግባቱ እንደ ስንዴ እና መሰል የግብርና ምርቶችን ከውጭ እያስገባች ኢኮኖሚዋን የምትደጉምን አገር ትልቅ ኪሳራ ላይ ይጥላል” ሲሉም አክለዋል።
“የመንግስት በጀት የጦርነት ወጪዎችን ለመሸፈን እየዋለ መሆኑ ጦርነቱ ያልተካሄደባቸውን ክልሎች ሳይቀር መጉዳቱ አይቀርም” ያሉት አቶ አማንይሁን ጦርነቱን በተቻለ መጠን በስምምነት አልያም በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የፌደራል መንግስት ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት ሁልጊዜ ከፍትህ እና ከእውነት ጎን እንደማይቆም ተረድቶ የተቀናጀ እና በባለሙያዎች የተመራ የዲፕሎማሲ ስራ ሊሰራ ይገባል ሲሉም ሀሳባቸውን ጠቁመዋል።
“ከዓለማችን ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ኢምባሲዎቿን በከፊል እዘጋለሁ ማለቷ ትልቅ ስህተት ነው” የሚሉት አቶ አማንይሁን፤ “መፍትሄው የዲፕሎማሲ ስራችን ለምን ስኬታማ አልሆነም? የሚለውን መፈተሽ ብቻ ነው” ብለዋል።
ህክምናቸውን እንዲከታተሉ፤ እንዲማሩ እና ጡረታቸውን አንዲያስከብሩ አምባሳደሮችን ስትሾም የቆየቸው ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራዎቿ ውጤታማ ባይሆኑ እንደማይገርማቸውም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ጫናዎችን መቀነስ የሚቻለው የዲፕሎማሲ እውቀት ያላችውን ባለሙያዎች በመመደብ፤ የላቀ የቋንቋ ብቃት እና ዓለም አቀፍ ቢሆኔዎችን መረዳት ከሚችሉ ሰዎች ጋር መስራት እና የጠራ የኮሙንኬሽን ስራዎችን በመስራት መሆኑን የፌደራል መንግስት መረዳት ይጠበቅበታል ሲሉም አቶ አማንይሁን ገልጸዋል።
የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ህወሃት) ጦርነት በየትኛውም ዓለም ችግር ሲፈታ አለመታየቱን አምኖ በጦርነት የተሰላቸውን እና ለጥቅሙ እቆምለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ ሲል ወደ ሰላም ሊመጣ ይገባልም ብለዋል አቶ አማንይሁን።
ህወሓት የትግራይ ህዝብን ወደ ጦርነት ማስገባቱ ስህተት መሆኑን አምኖ ሊቀበል ይገባል የሚሉት አቶ አማንይሁን የክልሉን ህዝብ ከሌሎች አቻ ክልሎች ወደኋላ እያስቀረው አምራች ሀይሉንም እያጣ መሆኑን ማሰብ እንዳለበትም ገልጸዋል።
አቶ ያሬድ ሀይለመስቀል ሌላኛው የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ምሁር ናቸው። እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በህወሀት ሜዳ እየተካሄደ ያለ ጦርነት በመሆኑ የጦርነት ሜዳውን መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።
የብሄርተኝነት ፖለቲካ እንደ ሳይክል ፔዳል የግድ መምታትን ይጠይቃል የሚሉት አቶ ያሬድ ህወሓት ያለ ጦርነት እና ግጭት መኖር የማይችል ስብስብ በመሆኑ መጋጨት ያቆመ ቀን ይሞታል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ “ህወሓት አይደለም ራያን እና ወልቃይትን ደሴን ወይም ጎጃምን ቢይዝም ጦርነት ሊያቆም አይችልም” ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ትግራይን መልቀቁ ትልቅ ስህተት ነበር የሚሉት አቶ ያሬድ፤ የፌደራል መንግስት ያገኘውን ድል በህዝብ ግንኙነት ስራው ተበልጦ እና ህወሀትን በማቃለሉ ኢትዮጵያን ዋጋ አስከፍሏል ሲሉ ገልጸዋል።
ህወሓት የነጮችን እና በጦርነቱ ያልተሳተፉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ድጋፍ ለማግኘት ረሀብ፣ አስገድዶ ደፈራ እና ሌሎች ልብ የሚነኩ ጉዳዮችን በማግነን ትኩረቶችን በመሳብ የተለያዩ ድጋፎችን ማግኘት መቻሉን አቶ ያሬድ ገልጸዋል።
በአንጻሩ የፌደራል መንግስት ግን የትግራይ ህዝብን ከህወሃት የሚነጥሉ ስራዎችን ከመስራት ይልቅ ስለ ህወሓት መደምሰስ እና ማቃለል ላይ ማተኮሩን አቶ ያሬድ ተናግረው ይህ የኢትዮጵያን መልካም ስም ማጉደፉን አንስተዋል።
መፍትሄው ጥርት ያለ የኮሙንኬሽን ሰንሰለት መዘርጋት፤ ዓለም አቀፍ ሎቢስቶችን በመቅጠር መንግስት እያደረገ ያለውን ስራ እንዲረዱ ከማድረግ አልፎ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማግባባት፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋማት እና አገራት ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረግ በግልጽ አቋማቸውን እንዲያሳውቁ ከማድረግ ጀምሮ የህውሓትን ድርጊት እንዲያወግዙ ማግባባት ለነገ የማይተው ስራ መሆኑንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ጥቅም ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሚኒስተሮች በግልጽ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በመቅረብ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ማስረዳት መልመድ እንዳለባቸውም አቶ ያሬድ አሳስበዋል።
የፌደራል መንግስት ይሄንን ሳያደርግ ቀርቶ እና ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ካላጠናቀቅ ግን በትርፉ እየተጫወተ ያለው ህወሓት አሸንፎ ኢትዮጵያም በዓለም መድረክ የተዋረደች አገር መሆኗ የማይቀር ነው ብለዋል።
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ስራዎች ድጋፍ ከጦርነቱ በጀት ውጪ 100 ቢሊየን በር ወጪ ማውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸው ይታወሳል።
በተለያዩ ክፍለ አህጉራት ካሏት ኢምባሲዎች በግማሽ ልተዘጋ እንደምትችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር።