“ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እብደት ነው” ፕሬዝደንት ኢሳያስ
በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ለሀገሪቱ እንደማይጠቅማትም አንስተዋል
“ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እብደት ነው” ፕሬዝደንት ኢሳያስ
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ ትናንት ምሽት ከሀገራቸው ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ከሁለት ዓመታት በፊት የኢትዮያና የኤርትራ የኦምሀጀር ድንበር በተከፈተበት ወቅት ከቀድሞው የትግራይ ክልል ር/መስተዳደር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው ለምን ለጦርነት ዝግጅት እንደሚያደርጉ ጠይቀዋቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡
ሕወሓት በፍጹም የሰሜን ዕዝን በማጥቃት ጦርነት ይጀምራል ብሎ የጠበቀ እንደሌለ የገለጹት ፕሬዝደንት ኢሳያስ "ይህ ጦርነት በተሳሳተ ስሌት የተጀመረ ነው” ያሉ ሲሆን “ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እብደት ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በረቂቅ ደረጃ ላይ እያለ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ረቂቁን በምስጢር አሳይተዋቸው እንደነበር በመግለጽ ሕገ-መንግስቱ በተለይም አንቀጽ 39 ለኢትዮጵያ እንደማይሆናት ነግረዋቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በትግራይ የተፈጠረው ጦርነት መንስዔም ከዓመታት በፊት የተቀበረ ፈንጅ ውጤት እንደሆነ ነው ፕሬዝደንት ኢሳያስ ያብራሩት፡፡ ሕገ መንግስቱ ለብሔር እና ለሀይማኖት አክራሪነት እንደሚዳርግ እና ቀጣይነት ያለው ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሕወሓት ዕቅድ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ የኢትዮጵያን መንግስት ካስወገደ በኋላ ኤርትራን መውረር እንደነበረም ገልጸዋል፡፡
አጠቃላይ በቀጣናው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እየተጠናከረ መምጣቱን በመጠቆም ጣልቃ ገብነቱ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሽግግር ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት በመካከላቸው የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ መካረሩ ሁለቱንም ሀገራት እንደሚጎዳም ነው ፕሬዝደንት ኢሳያስ የገለጹት፡፡ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል እየሆነ ያለው ነገር አስደንጋጭ እና አስገራሚ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይም የሦስቱንም ሀገራት ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ አፋጣኝ እልባት ማግኘት እንዳለበት አንስተዋል፡፡
በቀጣናው ከሚገኙ ሌሎች ሀገራት ይልቅ የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት “ይበልጥ የምንፈልገው እና የሚያሳስበን” ጉዳይ ነው ሲሉም ነው የገለጹት፡፡ በቀጣናው ትልቅ ሀገር የሆነችው የኢትዮጵያ ሰላም ለቀጣናው ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም ኤርትራ የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል በተካሔደው ውጊያ የኤርትራ ጦር ስለመሳተፍ አለመሳተፉ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ያሉት ነገር የለም፡፡ ምንም እንኳን በውጊያው ኤርትራ ጦሯን በማስገባት መሳተፏ በተለያዩ አካላት ቢገለጽም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ውንጀላውን አጣጥለዋል፡፡