ደቡብ ኮሪያ በፒዮንግያንግ ላይ በድሮን በራሪ ወረቀቶችን በትናለች ስትል ሰሜን ኮሪያ ከሰሰች
ሰሜን ይህን ድርጊት ወደ ጦርነት ሊያመራ የሚችል ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ትንኮሳ ነው ብላለች
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ ጥሰት የአጸፋ ምላሽ ያስፈልገዋል ብሏል
ደቡብ ኮሪያ በፒዮንግያንግ ላይ በድሮን በራሪ ወረቀቶችን በትናለች ስትል ሰሜን ኮሪያ ከሰሰች።
ሰሜን ኮሪያ፣ ደቡብ ኮሪያ በትናንትናው እለት በድሮን አማካኝነት ብዙ ቁጥር ያላቸው በራሪ ወረቀቶችን በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ ላይ በትናለች የሚል ክስ አቅርባለች።
ሰሜን ይህን ድርጊት ወደ ጦርነት ሊያመራ የሚችል ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ትንኮሳ ነው ብላለች።
የደቡብ ኮሪያ ጦር ባወጣው መግለጫ ሰሜን ኮሪያ ያቀረበችውን ክስ ባያረጋግጥም፣ ሰሜን ኮሪያ ቆሻሻ የጫኑ ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ የመላክ ልምድ እንዳላት ጠቅሷል።
ድሮኖቹ ባለፈው ሳምንት እና ከትናንት በስትያ በፒዮንግያንግ ሲበሩ እንደነበር የገለፈው የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ ጥሰት የአጸፋ ምላሽ ያስፈልገዋል ማለቱን ሮይተርስ የሰሜን ኮሪያውያን ኬሲኤንኤ ጠቅሶ ዘጎቧል።
"ደቡብ ኮሪያ ሁለቱን ወገኖች ወደ ጦርነት ሊያስገባ የሚችልን እንዲህ አይነት ኃላፊነት የጎደላው እና አደገኛ ትንኮሳ ማቆም አለባት" ብሏል ሚኒስቴሩ።
የደቡብ ኮሪያ ጦር በመግለጫው "በሰሜን ኮሪያ የቀረበውን ክስ እውነተኛነት ማረጋገጥ አይችልም" ብሏል።"በቅርቡ ለተፈጠሩ ተከታታይ ክስተቶች ኃላፊነቱን የምትወስደው ፒዮንግያንግ ነች።"
ሰሜን ኮሪያ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎች በመላክ በአለም አሳፋሪ ተግባር እየፈጸመች እና ሌሎች ትንኮሳዎችን እያደረገች ነው ያለው ሚኒስቴሩ በትናንትናው እለትም ተጨማሪ ፊኞችን መላኳን ገልጿል። ሰሜን ኮሪያ ከባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎችን በመላክ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት እንዲባባስ አድርጋለች።
የደቡብ ኮሪያ ጦር ባለስልጣን ከመንግስት ውጭ የሆነ የግል ቡድን በራሪ ወረቀቶችን ወደ ሰሜን ኮሪያ ልኮ እንደሆነ እየተጣራ መሆኑን ሮይተርስ የደቡብ ኮሪያውን ዮንሀፕ ዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
ባለፈው ታህሳስ ወር ሰሜን ኮሪያ ከ2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ድንበር በጣሰችበት ተግባር አምስት የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች የደቡብ ኮሪያን ድንበር ጥሰው መግባታቸው እና ሴኡል የጦር ጄቶቼን ለማሰማራት መገደዷ ይታወሳል።
ከ1950-53 የተደረገው የሁለቱ ኮሪያዎች የእርስ በእርስ ጦርነት በተኩስ አቁም ካበቃ በኋላ የሰላም ስምምነት ባለመኖሩ ምክንያት አሁንም ቅራኔ ውስጥ ናቸው።