የሰሜን ኮሪያ ጦር ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ እና የባቡር መስመር ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ መሆኑን ገለጸ
የጦሩ ውሳኔ በሁለቱ ሀገራት ወሰን አካባቢ ያለውን እንቅስቃሴ የበለጠ ውጥረት የተሞላበት እንዲሆን ያደርገዋል ተብሏል
ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት በተፈራረመችው ፒዮንግያንግ እና የአሜሪካ አጋር በሆነችው ሴኡል መካከል ያለው ውጥረት ሊረግብ አልቻለም
የሰሜን ኮሪያ ጦር ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ እና የባቡር መስመር ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ መሆኑን ገለጸ።
የሰሜን ኮሪያ ጦር ከደቡብ ኮሪያ የሚያገናኘውን መንገድ እና የባቡር መስመር ከዛሬ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንደሚዘጋ እና በእሱ በኩሉ ባሉት ቦታዎች ላይ ምሽግ እንደሚያጠናክር መግለጹን ሮይተርስ ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ዘግቧል።
የጦሩ ውሳኔ በሁለቱ ሀገራት ወሰን አካባቢ ያለውን እንቅስቃሴ የበለጠ ውጥረት የተሞላበት እንዲሆን ያደርገዋል ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ በዚህ አመት ከፍተኛ የወታደር ክምችት ባለባቸው የድንበር አካባቢዎች ላይ ፈንጆችን የማጥመድ፣ አጥር የማጠር እና ለእንቅስቃሴ የማይመች ረግረግ ቦታዎችን የመፍጠር ስራ ማከናወኗን የደቡብ ኮሪያ ጦር ባለፈው ሐምሌ ገልጿል።
እንደዘገባው ከሆነ የሰሜን ኮሪያ ጦር ይህን ያደረገው "በጠብ አጫሪዋ" ደቡብ ኮሪያ ለሚደረገው የጦር ልምምድ እና የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ የኑክሌር ተልእኮ ለሚያደርገው ተደጋጋሚ ጉብኝት ምላሽ ለመስጠት ነው።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው ጉዳዩን ለተመድ ኮማንድ ማሳወቁን ገልጿል። ሚኒስቴሩ አክሎም እንደገለጸው ደቡብ ኮሪያ ከተመድ ኮማንድ ጋር በቅርበት እየተነጋገረች ነው።
በአሜሪካ የሚመራው የተመድ ኮማንድ ከበርካታ ሀገራት የተውጣጣ ኃይል ሲሆን በሁለቱ ኮሪዎች መካከል በሚገኘው 'ዲሚሊታራይዝ ዞን' ወይም ከጦርነት ነጻ ቀጠና ያለውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ነው።
ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን ቀንደኛ ጠላት አድርጋ ፈርጃታለች።
የደቡብ ኮሪያን እና የአሜሪካን ወታደራዊ ልምምዶች እና ትብብሮች በስጋት የምትመለከተው ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር የጦር መሳሪያ መሀርሃግብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጽ አድርጋለች።
ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት በተፈራረመችው ፒዮንግያንግ እና የአሜሪካ አጋር በሆነችው ሴኡል መካከል ያለው ውጥረት ሊረግብ አልቻለም።