እድሜ ቁጥር ነው የሚሉት የ81 አመቷ የቁንጅና ተወዳዳሪ ደቡብ ኮርያዊት
አዛውንቷ ሀገራቸውን ወክለው በአለም የቁንጅና ውድድር ላይ ለመሳተፍ በተደረገው ማጣርያ ምርጥ 31 ውስጥ መካተት ችለዋል
በ72 አመታቸው ወደ ቁንጅና ውድድር እንደገቡ የሚነገርላቸው ግለሰቧ የፋሺን ሞዴል የመሆን ትልቅ ህልም አላቸው
ደቡብ ኮርያዊቷ የ81 አመት ባለጸጋ ቾይ ሱን ህዋ እድሜያቸው በ20ዎቹ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ነበር የፋሽን ሞዴል የመሆን ጽኑ ህልም የነበራቸው፡፡
ነገር ግን የህይወት ውጣ ወረድ እና ጫናዎች ግባቸውን ለማሳካት ተጨማሪ አምስት አስርት አመታትን እንዲጠብቁ አስገድዷቸዋል፡፡
አዛውንቷ ልጆቻቸውን ለመንከባከብ እና በገንዘብ ራሳቸውን ለመደጎም በወጣትነት ጊዜ ፋሽን ሞዴል ወይም የፊልም ተዋናይ የመሆን ህልማቸውን ወደ ጎን በመተው በሆስፒታል ውስጥ ተቀጥረው አብዘሀኛው ኑሯቸውን አሳልፈዋል፡፡
ብራማ ጸጉር ያላቸው የ81 አመቷ ቾይ በቅርቡ ለአለም ቁንጅና ውድድር ደቡብ ኮርያን ወክለው የሚወዳደሩ ቆንጆዎችን ለመምረጥ በተካሄደው ሚስ ዩኒቨርስ ኮርያ ላይ በእድሜ ትልቋ የቁንጅና ውድድር ተወዳዳሪ በመሆን ታሪክ መስራት ችለዋል፡፡
አዛውንቷ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ የቻሉት አወዳዳሪው አካል በማወዳደርያ መስፈርቱ ከ18-28 እድሜ ክልል ውስጥ ብቻ የሚገኙ ወይዛዝርት እንዲሳተፉ የሚጠይቃውን ህግ መሻሩን ተከትሎ ነው፡፡
በ72 አመታቸው የሞዴሊንግ ትምህርትን በመማር ምሽት ላይ በሚሰሩበት ሆስፒታል የእርምጃ እና አቋቋምን ይለማመዱ እንደነበር ሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡
ቀጥሎም በተለያዩ የፋሽን ትርዒቶች ላይ እና የአልባሳት ማስታወቂያዎች ላይ በሰፊው መታየት የጀመሩት ቾይ የመገናኛ ብዙሀን ቀልብን መሳባቸውን ተከትሎ የቁንጅና ውድድር የእድሜ መስፈርቶችን እስከማስቀየር የደረሰ ተጽዕኖ መፍጠር ችለዋል፡፡
በመጪው ጥር ወር በሜክሲኮ በሚካሄደው የአለም ቁንጅና ውድድር ለይ ደቡብ ኮርያን ወክሎ ለመሳተፍ በተደረገው ማጣርያ ምርጥ 31 ውስጥ መካተት ችለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም እስከመጨረሻው ዙር ውድድር ድረስ መድረስ የቻሉት አዛውንቷ በምርጥ አልባስ ተሸላሚ ሲሆኑ የ22 አመቷ የፋሽን ትምህርት ቤት ምሩቅ ደቡብ ኮርያዊት አንደኛ በመውጣት በጥቅምቱ ውድደር ሀገሯን የምትወክል ይሆናል፡፡
የ81 አመቷ ቾይ በዚህ እድሜየ የሁል ጊዜ ህልሜን ማሳካት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ ያሉ ሲሆን ወጣቶች ፍላጎት እና ህልማቸውን ለማሳካት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ተስፋ እንዳይቆርጡ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡