የሳተላይት ቅየራው የተካሄደው፣ የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን በፒዮንግያንግ ጉብኝት ካደረጉ እና ከመሪው ኪም ጋር ወታራዊ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው
ሰሜን ኮሪያ የቴሌቪዥን ስርጭቷን ወደ ሩሲያ ሳተላይት ቀየረች
ሰሜን ኮሪያ የመንግስት ቴሌቪዥን ስርጭቶች የሚተላለፉበትን ከቻይና ወደ ሩሲያ ሳተላይት መቀየሯን የደቡብ ኮሪያ ዩኒፊኬሽን ሚኒስቴር ገልጿል።
ይህ ክትትል ለሚያደርጉ የደቡብ ኮሪያ የመንግስት ኤጀንሲዎች እና ሚዲያዎች አስቸጋሪ ያደርገዋል ተብሏል።
የሰሜን ኮሪያ ሴንትራል ቴሌቪዥን ስርጭት ቀደም ሲል ይተላለፍ የነበረበትን ቻይናሳት12 ሳተላይት በመተው በሩሲያው ኤክፕረስ103 ሲተላለፍ መታየቱን ሮይተርስ የደቡብ ኮሪያውን የዲሽ አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
የሳተላይት ቅየራው የተካሄደው፣ የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በፒዮንግያንግ ጉብኝት ካደረጉ እና ከመሪው ኪም ጆንግ ኡን ጋር ወታራዊ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።
የሰሜን ኮሪያን ቴሌቪዥን አሁንም በኦንላይን ማየት ቢቻልም፣ ጥራቱ አነስኛ ነው።
የሚተላለፉት ይዘቶች በእቅድ የተዘጋጁ እና ፓለቲካዊ ቢሆኑም ዝግ ከሆነቸው ሀገር የሚገኘው መረጃ ውስን ስለሆነ የደቡብ ኮሪያ መንግስት እና ሚዲያዎች የሰሜን ኮሪያን ሚዲያዎች ይከታተላሉ።
ሰሜን ኮሪያ የቴሌቪዥን ስርጭቷን ወደ ሩሲያ ሳተላይት ካዛወረች በኋላ የሳተላይት ስርጭቱ በተወሰኑ የደቡብ ኮሪያ ቦታዎች እንደማይሰራ የገለጸው የዩኒፊኬሽን ሚኒስቴሩ የቴክኒክ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አክሎ ገልጿል።
በደቡብ ኮሪያ የተፈቀደላቸው አካላት የሰሜን ኮሪያን ሚዲያዎች ይመለከታሉ፤ የደቡብ ኮሪያ ህዝብ ግን እንዲያይ አይፈቀድለትም።
ሩሲያ በአሜሪካ የሚመራውን የምዕራባውያን ጥምረት ለመገዳደር ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ስታሳድግ፣ ቻይና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያወሳስብ የሚችል ስምምነት ከማድረግ ታቅባለች።
ፑቲን እና ኪም በቅርብ በፒዮንግያንግ በፈረሙት የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት፣ ጥቃት በሚሰነዘርባቸው ወቅት አንዳቸው ለሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ወታደራዊ ድጋፍ ይሰጣል።