ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ስምምነት ላይ የደረሱባቸው ቁልፍ የትብብር ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
በከፍተኛ የአለም አቀፍ መገለል ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ሀገራት በበርካታ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል
ሀገራቱ ወታደራዊ አጋርነትን ጨምሮ በአለምአቀፍ ጂኦፖለቲክስ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንቆማለን ብለዋል
ከሰሞኑ በሰሜን ኮሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፒዮንግያንግ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ቬትናም አምርተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሰሜን ኮሪያ በነበራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ መሪ ኪሚ ጆንግ ኡን ጋር የጋራ በሚያደረጓቸው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት በአይነቱ ጠንከር ያለ ሁለገብ ስትራቴጂካዊ የጋራ ትብብር ስምምነትን ተፈራርመዋል፡፡
ከስምምነቱ ነጥቦች መካከል ሀገራቱ አንዱ በሌላኛው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ላመለግባት ሉአላዊነትን ያከበረ የጋራ ወዳጅነትን ማስቀጠል የሚያነሰው ነጥብ ቀዳሚው ነው፡፡
በአንደኛው ሀገር ላይ ጥቃት ቢከፈት ለመተጋገዝ እንዲሁም በምዕራቡ አለም የሚዘወረውን ባለአንድወገን የአለም ስርአት ለመቀየረ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የአንዱን ሀገር ጥቅም የሚጎዳ ፣ ሉአላዊነትን የሚጋፋ እና ብሄራዊ ደህንነትን ስጋት ላይ የሚጥል ግንኙነትን ከሌሎች ሀገራት ጋር ላለማድረግ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ላይ የጋራ አቋሞችን ለማንጸባረቅ እና ለመተጋገዝ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ሀገራቱ በምግብ፣ ኢነርጂ፣ የደህንት እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖለጂ ልማት ላይ መተባበር በተጨማሪም በንግድ ፣ ኢንቨስትመንት ፣ ቱሪዝም እና ሳይንስ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ወጥነዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ልማትን በተመለከተ የኒውክሌር ኢነርጂ ፣ የስፔስ ሳይንስ ፣ ባዮሎጂ ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ላይ በጋራ መስራትን የስምምነቱ አንቀጾች አካተዋል፡፡
ግብርና ፣ስፖርት ፣ ጤና ፣ ትምህርት ፣ እንዲሁም አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን የተመለከቱ የጋራ አውደርእዮችን እና ሁነቶችን በቀጣይ ለማዘጋጀት በቅርቡ የጋራ ኮሚቴ ያቋቁማሉ፡፡
በህግ ጉዳዮች ላይ፣ የጸጥታ እና ደህንነት እንዲሁም የፖሊስ አባላት ስልጠና ፣የእጽ አዘዋዋሪ እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ እንዲሁም ሽብርተኝነትን መከላከልን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ከፈረሙት ስትራቴጂካዊ ስምምነት ውስጥ በአንድኛው ሀገር ላይ ጦርነት በታወጀ ጊዜ የጦር መሳርያ እና ወታደራዊ ድጋፍን ለማድረግ የደረሱት ስምምነት የአለምን ትኩረት ስቧል፡፡
ጃፓን ወታደራዊ ስምምነቱ በቀጠናው ተጨማሪ ውጥረትን የሚፈጥር ነው ስትል የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሃፊ ደግሞ የአምባገነኖችን መሰባሰብ የሚያሳይ ስምምነት ሲሉ ገልጸውታል፡፡