የሰርግ ቬሎ፣ መነጸር እና ጅንስ ሱሪ የምትከለክለው ሰሜን ኮርያ
መንግስት የውጭ ተጽእኖን ለመከላከል በሚል የከለከላቸውን ቁሳቁሶች ፍለጋ ቤት ለቤት አሰሳ እያደረገ ይገኛል
የኪም አስተዳደር በ2020 ባወጣው ህግ የደቡብ ኮርያ ሙዚቃ አና ፊልም መመልከት በሞት የሚስቀጣ ወንጀል ነው
በመላው ሰሜን ኮርያ ከፍተኛ የተባለ የቤት ለቤት አሰሳ እየተደረገ ነው፡፡ የውጭ ባህል ተጽእኖን ለመከላከል በሚል በወጣው ህግ መሰረት ሀገሪቱ በተለያዩ የመገልገያ ቁሶች ላይ ክልከላ አድርጋለች፡፡
ለብዙዎች ግራ የሚያጋቡት የሰሜን ኮርያ ህጎች የሰርግ ነጭ ቬሎ ፣ መነጻር እና ጅንስ ሱሪን ማድረግ ይከለክላሉ፡፡
በደቡብ እና ሰሜን ኮርያ መካከል ያለውን ውጥረት ተከትሎ የደቡቡን ሙዚቃ እና ፊልሞችን መመለክት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጎ የደነገገው የኪም አስተዳደር ከሰሞኑ አዲስ ሀገር አቀፍ የቤት ለቤት ብርበራ ጀምሯል፡፡
በባለፈው አመት 70 የደቡብ ኮርያ ሙዚቃዎችን እና 3 የደቡብ ኮርያ ፊልሞችን የተመለከተች የ22 አመት ሰሜን ኮርያዊት ወጣት ህዝብ በተሰበሰበበት በሞት ተቀጥታለች፡፡
በተመሳሳይ አመት ሁለት ታዳጊዎች ሙዚቃ ሲሰሙ ተገኝተው ከፍተኛ የጉለበት ስራ ወደ ሚሰራበት ስፍራ እንደተላኩ ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ ቁጥራቸው 2 ሺህ የሚጠጉ “አስቀያሚ” ቆሻሻ የተሸከሙ ፊኛዎችን ወደ ደቡቡ የላከችው ሰሜን ኮርያ መሰል የፕሮፖጋንዳ ጥቃቶችን እንደምትቀጥልባቸው ዝታለች፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ መልክ ቤት ለቤት ተጀምሯል የተባለው ብርበራም ከዚሁ ጋር በተገናኝ የደቡብ ኮርያ የማህበረሰብ አንቂዎች ወደ ሰሜን ልከውታል የተባለውን ቁሳቁስ ለማደን ነው ተብሏል፡፡
ከ2021 ጀምሮ የደቡብ ኮርያ የማህበረሰብ አንቂዎች ለሰሜን የፕሮፖጋንዳ ጥቃት በሚሰጡት ምላሽ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፊኛዎችን ወደ ሰሜን ኮርያ ልከዋል፡፡
ፊኛዎቹ ፒዮንግያንግ የከለከለቻቸውን የደቡብ ኮርያ ፊልም እና ሙዚቃዎች ፣ ጅንስ ሱሪ ፣ የሰርግ ቬሎ ቀሚስ ፣ መነጸር ፣ ገንዘብ ፣ ቼኮሌት እና ሌሎችንም ቁሶች የያዙ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት ቤት ለቤት ከሚደረገው ፍተሻ ባለፈ የሰሜን ኮርያውያን የእጅ ስልኮች የተለዋወጧቸው የጽሁፍ መልእክቶች እና የተደዋወሏቸው ስልኮች ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በሰሜን ኮርያ ተግባራዊ ከሚደረጉ ሌሎች አስገራሚ ህጎች መካከል ኢንተርኔት መጠቀም አይቻልም ፣ አባት ጥፋት ካጠፋ ቅጣቱ እስከ ሶስት ትውልድ ይተላለፋል ፣ መሪው ኪሚ ጆንግ ኡን የሚቆረጡትን አይነት የጸጉር ቁርጥ መቆረጥ ክልክል ነው ፣ ማሪዋና የተባለውን እጽ ማጨስ፣መግዛት፣መሸጥ ይፈቀዳል የሚሉት ይገኙበታል።