ሰሜን ኮሪያ 1 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ክሪፕቶከረንሲ ዘርፋለች ሲል የመንግስታቱ ድርጅት ገለጸ
ፒዮንግያንግ የቀጠረቻቸው የመረጃ መንታፊዎች በአለም አቀፍ ተቋማት ላይ የሚያደርሱት የሳይበር ጥቃትም እየጨመረ እንደሚገኝ ተገልጿል
ላዛረስ ግሩፕ፣ አንዳሪየል እና ኪምሳኪ በሚል መጠሪያ የሚንቀሳቀሱት የመረጃ ዘራፊ ቡድኖች በሰሜን ኮሪያ የደህንነት ቢሮ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ በ2022 የዘረፈችው ክሪፕቶከረንሲ ወይም የዲጂታል ገንዘብ ከምንጊዜውም የበለጠ ነው አለ የመንግስታቱ ድርጅት።
ፒዮንግያንግ የዲጂታል ገንዘብ ለመዝረፍም ሆነ ከተቋማት ወሳኝ መረጃዎችን ለመመንተፍ የምትጠቀማቸው የሳይበር ቴክኖሎጂዎች እየዘመኑ መሄዳቸውንም ነው በሰሜን ኮሪያ የተጣሉ ማዕቀቦችን የሚቆጣጠረው ቡድን ሪፖርት የሚያሳየው።
ቡድኑ ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርቱ ሰሜን ኮሪያ በ2022 ከ630 ሚሊየን ዶላር እስከ 1 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የዲጂታል ገንዘብ (ክሪፕቶከረንሲ) መዝረፏን አመላክቷል።
የመረጃ መንታፊዎቹ የሚጠቀሟቸው ዘዴዎች እየተራቀቁ መምጣት የተዘረፈው የዲጂታል ገንዘብ መዳረሻ ለመከታተል አስቸጋሪ እንዳደረገው ያሳያል ሪፖርቱ።
አብዛኛውን የሳይበር ጥቃት እና የዲጂታል ገንዘብ ዘረፋ የሚፈጽሙት ላዛረስ ግሩፕ፣ ኪምሳኪ እና አንዳሪያል የተሰኙት ቡድኖችም በሰሜን ኮሪያ የደህንነት መስሪያ ቤት ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው የመርማሪ ቡድኑ ጠቁሟል።
ፒዮንግያንግ ለኒዩክሌር መሳሪያ ልማቷ ይጠቅማሉ የምትላቸውን መረጃዎችም በነዚህ ቡድኖች አማካኝነት እንደምታዘርፍ መገለጹንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ቡድኖቹ ቫይረስ የያዙ የኢሜል መልዕክቶችን በመስደድ የበርካታ ሀገራት ተቋማትን የሳይበር ጥቃት ኢላማ ማድረግ ላይ ተጠምደዋል ተብሏል።
ሆሊጎስት የተሰኘ ከፒዮንግያንግ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድንም የተለያዩ ሀገራት ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት በማድረስ የያዛቸውን መረጃዎች ለመልቀቅ ሚሊየን ዶላሮችን እየጠየቀ ስለመሆኑም ተጠቅሷል።
የመንግስታቱ ድርጅት በ2019 ባወጣው መረጃ ፒዮንግያንግ በሳይበር ጥቃት ያገኘችውን 2 ቢሊየን ዶላር ለኒዩክሌር ሃይል ልማቷ ማፋጠኛ አድርጋዋለች ብሏል።
ድርጅቱ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ ላዛረስ የተሰኘው የመረጃ መንታፊ ቡድን ሃብቱን እንዳያንቀሳቅስ ማዕቀብ ለመጣል ውሳኔ ሃሳብ ቢያቀርብም ቻይና እና ሩሲያ ሳይቀበሉት መቅረታቸው ይታወሳል።
ላዛረስ በ2017 በ150 ሀገራት ከ300 ሺህ በላይ ኮምፒውተሮችን ላጠቃው “ዋናክራይ” የተባለ የሳይበር ጥቃት ተጠያቂ ይደረጋል።
አሜሪካ እና ብሪታንያም ከዚህ የአለም መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ከነበረ የሳይበር ጥቃት ጋር በተያያዘ የሰሜን ኮሪያ እጅ እንዳለበት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።