አሜሪካ በኮሪያ ልሳነ ምድር “ቀይ መስመሩን እያለፈች ነው”- ሰሜን ኮሪያ
ፒዮንግያንግ፥ ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ለሚያደርጉት ወታደታዊ ልምምድ “ከብድ ያለ” ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች
ዋይትሃውስ በበኩሉ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ግንኙነቱን የማሻከር ፍላጎት እንደሌለው አስታውቋል
አሜሪካ በኮሪያ ልሳነ ምድር የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ቀጠናውን ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ሰሜን ኮሪያ ገልጻለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር እያደረገች ያለችው ወታደራዊ ልምምድ “ቀይ መስመሩን ያለፈ” ነው ብሎታል።
የኮሪያ ልሳነ ምድርን ዋነኛ የጦር ቀጠና ለማድረግ የሚካሄደውን እንቅስቃሴም ተቃውሟል።
- የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልማት ስድስት እውነታዎች
- ሰሜን ኮሪያ፤ “አሜሪካ ወደ ዩክሬን ታንኮችን በመላክ ቀዩን መስመር የበለጠ እያለፈች ነው” አለች
የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የጦር አውሮፕላኖች በትናንትናው እለት ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል።
ይህን ልምምድም ጸብ አጫሪነት ነው ብላ የምታምነው ፒዮንግያንግ፥ አስፈላጊ ከሆነ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎቼን ተጠቅሜ አጻፋውን እመልሳለሁ በሚል ዝታለች።
ዋሽንግተን ቀጠናውን ከሚያተራምስ እርምጃዋ እስካልታቀበች ድረስም ለንግግር ዝግጁ እንደማትሆን ነው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ያመላከተው።
ዋይትሃውስ በበኩሉ “ከፒዮንግያንግ ጋር ግጭት የሚፈጥር ድርጊት አልፈጸምንም፤ አሁንም የምንሻው ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄን ነው” ብሏል።
“የሰሜን ኮሪያን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ልማት ለመግታት በጸጥታው ምክር ቤት የተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ከአጋሮቻችን ጋር መስራታችን እንቀጥላለን” የሚል መግለጫንም አውጥቷል።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን በዚህ ሳምንት በደቡብ ኮሪያ ባደረጉት ጉብኝትም ማጠናከራቸው የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ሀገራት የሰሜን ኮሪያን የኒዩክሌር ግስጋሴ ለማስቆም ወታደራዊ አጋርነታቸውን ማጥበቃቸው ፒዮንግያንግን አስቆጥቷል።
ቁጣዋንም ባለፈው አመት ብቻ ከ60 በላይ የሚሳኤል ሙከራዎችን በማድረግ መግለጿን ነው ሬውተርስ ያስታወሰው።
ከ28 ሺህ በላይ የአሜሪካ ወታደሮች የሚገኙባትና ከዋሽንግተን “ኒዩክሌር እናስታጥቅሻለን” ቃል የተገባላት ደቡብ ኮሪያ፥ ለዛሬው የጎረቤቷ ዛቻና ወቀሳ ምላሽ አልሰጠችም።