ፒዮንጊያንግ በኮሪያ ልሳነ ምድር ለተደቀነው ስጋት ዋሽንግተን ተጠያቂ አድርጋለች
ወታደራዊ ልምምዷን አጠናክራ የቀጠለችው ሰሜን ኮሪያ ለጦርነት ዝግጁ መሆኗ አስታወቀች፡፡
የደቡብ ኮሪያ የዜና ወኪል ዮንሃፕ የሰሜን ኮሪያ ሚዲያን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ፒዮንጊያንግ ለጦርነት ዝግጁ ናት ብለዋል።
ኪም ጆንግ ኡን ይህ ያሉት የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ሰብስበው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ "ሀገሪቱ የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ በማጠናከር ለጦርነት እንዘጋጃለን " ሲሉ መናገራቸውም ነው የተዘገበው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋሽንግተን አጋሮቿ እያደረጉት ያለውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የቀጠናውን ሁኔታ ወደ “ቀይ መስመር” እንደወሰደው በተለያዩ ጊዜያት ስትናገር ቆይታለች፡፡
የሰሜን ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “የጋራ ልምምዱ የኮሪያን ልሳነ ምድር ወደ ጦር ቀጠና የመቀየር ስጋት የደቀነ ነው” ብሎታል፡፡በተለይም አሜሪካ በቀጠናው የምታደረግው እንቅስቃሴ እጅግ አደገኛና ተንኳሽ መሆኑን በመግለጽ፡፡
“አሜሪካ የጥላቻ ፖሊሲዎችን እስከተከተለች ድረስ ፒዮንግያንግ የውይይት ፍላጎት የላትም ፣ እናም ሰሜን ኮሪያ ማንኛውንም የአሜሪካን ወታደራዊ እርምጃ ለመመከት ዝግጁ ናት ፣ አስፈላጊ ከሆነም የኒውክሌር ኃይልን ጨምሮ ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ስትራቴጂዎች አሏት” ሲልም አክሏል ሚኒስቴሩ።
ፒዮንጊያንግ ይህን ትበል እንጅ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተንኳሽ ነው የሚለውን ውንጀላ አሜሪካ እንደማትቀበለው ዋይትሃውስ በሰጠው ምላሽ አስታውቋል፡፡
“በሰሜን ኮሪያ ላይ ምንም ዓይነት የጥላቻ ዓላማ የለንም” ነው ያለቸው አሜሪካ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰሜን ኮሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲንን የደቡብ ኮሪያን ጉብኝት ተችቷል።
መከላከያ ሚኒስትሩ በሴኡል ቆይታቸው ከደቡብ ኮሪያ አቻቸው ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስትሮቹ ከፒዮንጊያንግ ሊቃጣ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የሚያደርጉትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማስፋትና እንደ አውሮፕላን ተሸካሚዎች የጦር መርከቦች እና የረዥም ርቀት ቦምብ ጣይ ጄቶች ያሉ ተጨማሪ "ስትራቴጂክ ወታደራዊ የጦር መሳሪያዎች" ለማሰማራትም ከስምምነት መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡
የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ ሰሜን ኮሪያን ኢላማ ያደረገ እንደሆነ በወቅቱ የተጠየቁት የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ኦስቲን “የአሜሪካ አላማ የበለጠ ደህንነትን እና መረጋጋትን ማስፈን ነው፤ ነገር ግን ደቡብ ኮሪያን ለመከላከል ቁርጠኛ ነን” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡
የቆየው የሁለቱ ኮሪያዎች ፍጥጫ ለወታደራዊ ልምምድ በሚል ሽፋን የአሜሪካ ወደ ቀጠናው ብቅ ከማለት ጋር ተዳምሮ፤ በኮሪያ ልሳነ ምድር አዲስ ቀውስ እንዳያመጣ ተሰግቷል፡፡