ሰሜን ኮሪያ ወደ ምስራቅ የባህር ክልሏ የባላስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፏ ደቡብ ኮሪያ ገለጸች
ፒዮንጊያንግ ያስወነጨፈችው ሚሳዔል ከጃፓን የኢኮኖሚ ዞን ውጪ ወድቆ ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸ ነው
የባላስቲክ ሚሳዔል ሙከራው የፈረንጆቹ 2022 ከገባ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ19ኛ ጊዜ የተደረገ ነው
ሰሜን ኮሪያ፤ ጃፓን እና ሁለቱም ኮሪያዎች ወደሚያዋስነው የምስራቅ ባህር ክልል የባላስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፏ የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታወቀ፡፡
ሰሜን ኮሪያ የባላስቲክ ሚሳዔሉን ያስወነጨፈችው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባሉበት እንዲሁም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ ቀጠናውን ይጎበኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት መሆኑ ከፍተኛ ስጋት ጭሯል፡፡
የአሜሪካ ባላስልጣናት፤ ከሃሪስ ጉዞ ጋር ለመገጣጠም የሚደረግ ማንኛውም የሚሳዔል ሙከራ ካለ "ለኮሪያ ሪፐብሊክና ለጃፓናውያን አጋሮቻችን ደህንነት” ሲባል አሜሪካ እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ጥቃቱ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ፒዮንግያንግ ከባህር ሰርጓጅ መርካብ የባሊስቲክ ሚሳዔል ለማስወንጨፍ በዝግጅት ላይ መሆኗና ምልክቶች መኖራቸው ሲዘግቡ መቆየታቸውን ተከትሎ የተሰነዘረ እንደሆንም ነው የተገለጸው፡፡
የተወነጨፍው ሚሳዔል ከጃፓን የኢኮኖሚ ዞን ውጪ ወድቆ ሊሆን እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮሪያ መሰል የባላስቲክ ሚሳዔል ሙከራዎችን ስታደረግ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ-ዮል በግንቦት ወር ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ወደ ምስራቅ ባህር ክልሏ ለመጨረሻ ጊዜ የባላስቲክ ሚሳዔል ያስቀነጨፈችው ባሳለፍነው ወርሃ ሰኔ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በአንድ ቀን ብቻ ስምንት የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ያስቀነጨፈችበት አጋጠሚ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
ሰሜን ኮሪያ አሁን ያካሄደችው የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራ ጨምሮ የፈረንጆቹ 2022 ከገባ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ19ኛ ጊዜ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ሰሜን ኮሪያ የምታስወነጭፋቸው ሚሳዔሎቹ ከምድር ከ25 እስከ 90 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ከ110 እስከ 600 ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት እንደሚበሩ ይነገራል፡፡