ኪም ጆንግ ኡን የሰሜን ኮሪያን "የኒውክሌር የታጠቀች ሀገር" ሲሉ አወጁ
የሀገሪቱ ፓርላማ በአደጋ ወቅት በጠላት ኢላማዎች ላይ የኒውክሌር ጥቃት እንድትፈጽም የሚፈቅ ህግ አጽድቋል
በኒውክሌር ጉዳይ ድርድር የለም ያሉት ኪም ጆንግ ኡን “ሰላም ሊገኝ የሚችለውም በኃይል ብቻ ነው" ብለዋል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሀገራቸውን "የኒውክሌር የታጠቀች ሀገር" ሆናለች ሲሉ አወጁ፡፡
ኪም ጆንግ ኡን ሊቀለበስ የማይችል ነው ባሉት ውሳኔያቸው፤ ሀገራቸው የኒውክሌር የታጠቀች ሀገር የሆነችበትን አዲስ ህግ ይፋ አድርገዋል።
" ሀገራችን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ሆናለች" ብለዋል ኪም ጆንግ ኡን።
"በአዲሱ ህግ መሰረት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቻችን ጉዳይ መደራደር የማይታሰብ ነው፤ ሰላም ሊገኝ የሚችለውም በኃይል ብቻ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
"ሀገራችንን ከኒውክሌር ነፃ ለማድረግ ምንም አይነት ድርድር አይኖርም" ሲሉም ነው የተደመጡት ኪም ጆንግ ኡን፡፡
የሀገሪቱ ፓርላማም ዛሬ ረፋድ ላይ ሀገሪቱ አደጋዎች በሚጋረጡባት ወቅት በጠላት ኢላማዎች ላይ የኒውክሌር ጥቃትን እንድትጀምር የሚፈቅደውን ህግ አጽድቋል፡፡
በዚህም ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መያዝን እንደ ህጋዊ ጉዳይ ፣አስፈላጊና መሰረታዊ መብት አድርጋ በመመልከት ባጸደቀችው አዲስ ህግ ራሷን “የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ያላት ሀገር” መሆኗ አውጃለች ሲል የኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
ነገር ግን በአዲሱ ህግ መሰረት የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ከማንም ጋር እንደማትጋራ እንዲሁም የአቶሚክ ቴክኖሎጂ እና ቁሳቁስ እንደማታስተላልፍም አስታውቃለች።
ሰሜን ኮሪያ ከ2017 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ታዛቢዎች እየገለጹ ነው።
እንደፈረንጆቹ በ2018 የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና ሌሎች መሪዎች ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ማበልጸጓን እንድትተው ኪም ጆንግ ኡንን ለማሳመን ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ የሚታወስ ነው፡፡