ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል አስወነጨፈች
ፒዮንግያንግ የአየር ክልሌን ጥሳለች ያለቻትን አሜሪካ ባስጠነቀቀች ማግስት ነው ሚሳኤሉን የተኮሰችው
ሙከራውን ተከትሎ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል
ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ እንደሆነ የተጠረጠረ ሚሳኤል ማስወንጨፏን ተነገረ።
ከፒዮንግያንግ የተተኮሰው ሚሳኤል ከ1 ስአት በላይ 1 ሺህ ኪሎሜትር የተምዘገዘገው ሚሳኤል በጃፓን ምዕራባዊ ክፍል በሚገኝ ባህር ውስጥ መውደቁን ነው የጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ያስታወቁት።
ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ማለዳ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሉን ያስወነጨፈችው አውሮፕላኗ የአየር ክልሌን ጥሷል ባለቻት አሜሪካ ላይ እርምጃ እንደምትወስድ በዛተች በቀናት ልዩነት ነው።
ዋሽንግተን የቅኝት አውሮፕላኖቿ የሰሜን ኮሪያን የአየር ክልል አለመጣሳቸውንና የአለም አቀፉን ህግ ማክበራቸውን ብትጠቅስም ፒዮንግያንግ አውሮፕላኖቹን እንደምትመታ መዛቷ ይታወሳል።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግ የአሜሪካ አውሮፕላኖች የሰሜን ኮሪያን የአየር ክልል መጣሳቸውን ከቀጠሉ ውጤቱ “አስደንጋጭ” ይሆናል ማለታቸውም አይዘነጋም።
የዛሬውን የሚሳኤል ሙከራ ተከትሎም የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን፥ የጋራ መግለጫ ማውጣታቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
“የሰሜን ኮሪይ የሚሳኤል ሙከራ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ብሎም የአለማቀፉን ማህበረሰብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ የመንግስታቱ ድርጅትን ህግጋትም ይቃረናል” በማለትም ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
የኔቶ ስብሰባን ለመታደም በሊትዩኒያ የሚገኙት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልም የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤታቸውን ለአስቸኳይ የበይነ መረብ ስብሰባ መጥራታቸው ነው የተነገረው።
ሰሜን ኮሪያ በሰኔ ወር አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ላካሄዱት ወታደራዊ ልምምድ ተቃውሞ አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ካስወነጨፈች ወዲህ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ፒዮንግያንግ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ለመጨረሻ ጊዜ ያስወነጨፈችውም በየካቲት ወር 2023 እንደነበር ይታወሳል።
ሀገሪቱ በሀምሌ ወር መጨረሻ የድል ቀኗን ስታከብርም አዳዲስ የጦር መሳሪያዎቿን እንደምታሳይ ነው የሚጠበቀው።