ሰሜን ኮሪያ የአየር ክልሏን የሚጥሱ የአሜሪካ "የስለላ አውሮፕላኖችን" ልትመታ እንደምትችል አስጠነቀቀች
ሰሜን ኮሪያ ሰኞ እለት አሜሪካ የአየር ክልሏን እንደጣሰች አስታወቀች
ፒዮንግያንግ የአሜሪካ ቀስቃሽ ወታደራዊ እርምጃ የኮሪያን ልሳነ ምድር ወደ ኒውክሌር ግጭት እያቀረበው ነው አለች
ሰሜን ኮሪያ ሰኞ እለት አሜሪካ የአየር ክልሏን እየጣሰች ነው ስትል ከሳለች።
ዋሽንግተን በአየር ክልሌ የክትትል በረራዎችን እያደረገች ነው ያለችው ፒዮንግያንግ፤ እንዲህ አይነት በረራዎችን ልትመታ እንደምትችል አስጠንቅቃለች።
የአሜሪካ ቀስቃሽ ወታደራዊ እርምጃዎች የኮሪያን ልሳነ ምድር ወደ ኒውክሌር ግጭት እያቀረበው ነው ሲሉ የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ መከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ቃል አቀባዩ አሜሪካ የስለላ አውሮፕላኖችንና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መጠቀሟን ጠቅሰው፤ ዋሽንግተን በልሳነ ምድሩ አቅራቢያ የኒውክሌር ሰርጓጅ መርከብ በመላክ ውጥረቷን እያባባሰች ነው ብለዋል።
መግለጫው ያለፈውን ክስተት በመጥቀስም፤ ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበርና በባህር ዳርቻ ላይ የአሜሪካ አውሮፕላኖችን በጥይት "መምታቷንና መጥለፏን" ገልጿል።
ፒዮንግያንግ በኮሪያ ልሳነ ምድር አቅራቢያ ስለሚደረጉ የአሜሪካ የስለላ በረራዎች ብዙ ጊዜ ቅሬታ አቅርባለች።
ሮይተርስ በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቆ አፋጣኝ ምላሽ አላገኘሁም ብሏል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር በበኩሉ ሰሜን ኮሪያ የአየር ክልል ተጥሷል ማለቷ ትክክል አይደለም ብሏል።
የአሜሪካ የአየር የክትትል በራሪዎች በአካባቢው ዙሪያ መደበኛ የስለላ በረራዎችን እንደሚያካሂዱ ገልጾ፤ አጋሮቹ ሰሜን ኮሪያን ለመከታተል በቅርበት እንደሚሰሩ ተናግሯል።