ኢራን የመጀመሪያ ሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤሏን አስተዋወቀች
“ፋታህ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል በስአት 15 ሺህ ኪሎሜተር ይምዘገዘጋል ተብሏል
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሉ የአሜሪካ እና እስራኤል የሚሳኤል መቃወሚያዎችን አልፎ ጥቃት ማድረስ እንደሚችልም ቴህራን ገልጻለች
ኢራን የመጀመሪያውን ሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤሏን ለእይታ ማቅረቧ ተነገረ።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ኢርና እንዳስነበበው፥ “ፋታህ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ዛሬ በይፋ ተዋውቋል።
ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና የአብዮት ዘብ ጠባቂው ከፍተኛ አመራሮችም የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሉን መጎብኘታቸው ተገልጿል።
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከድምጽ በአምስት እጥፍ የሚልቅ ፍጥነት አላቸው፤ ይህም ከእይታ ውጭ እንዲሆኑና ተመተው እንዳይወድቁ ያደርጋቸዋል።
ኢራን ዛሬ ያስተዋወቀችው “ፋታህ” ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልም በስአት 15 ሺህ ኪሎሜትር መምዘግዘግ እንደሚችል ነው የተነገረው።
“ፋታህ” የጠላትን ጸረ ሚሳኤሎች ማደባየት” ይችላል ያለው የኢራን ቴሌቪዥን “የአሜሪካንም ሆነ የእስራኤል የሚሳኤል መቃወሚያዎች አልፎ ኢላማውን መምታት” እንደሚችልም ዘግቧል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ተቃውሞ ቢቀጥልም ቴህራን የመከላከል አቅሜን ለማጠናከር የሚሳኤል ፕሮግራሜን እገፋበታለሁ ማለቷን ሬውተርስ ዘግቧል።
ምዕራባውያን የወታደራዊ ጉዳይ ተንታኞች የኢራን የሚሳኤል አቅም ከልክ በላይ ተጋኖ እንደሚቀርብ ቢያምኑም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) አዲሱ የኢራን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልእንዳሳሰበው ገልጿል።
የኢራን የባለስቲክ ሚሳኤል ልማት አሜሪካ በ2018 ከኢራን የኒዩክሌር ስምምነት እንድትወጣ ምክንያት መሆኑም የሚታወስ ነው።
ትራምፕን የተኩት ባይደን ወደ ኒዩክሌር ስምምነቱ ለመመለስ ሲያደርጉት የነበረው ሙከራም ከተቋረጠ ወራት ተቆጥረዋል።