አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ አዲስ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል
ሰሜን ኮሪያ ለሙከራ የተኮሰችው ሚሳኤል ከተመታ ጦርነት እንደምትጀምር አስጠነቀቀች።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ አዲስ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ሁለቱን ሀገራት አስጠንቅቃለች።
ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ባሊስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ላይ ያለችው ሰሜን ኮሪያ ወደ ፓስፊክ ውቂያኖስ የምተኩሳቸውን ሚሳኤሎች ማንም መንካት አይችልም ብላለች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን እህት የሆነችው ኪም ዮ ጆንግ እንዳሉት "ሰሜን ኮሪያ ለሙከራ የምተኩሳቸው ሚሳኤሎች ከተመቱ እና አቅጣጫቸውን እንዲስቱ ከተደረጉ ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ ወደ ጦርነት እናመራለን" ብለዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በቅርቡም ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ሚሳኤል ወደ ፓስፊክ ውቂያኖስ ለሙከራ እንደምትተኩስም ተገልጿል።
አሜሪካ እና አጋሯ ደቡብ ኮሪያ እስካሁን ከሰሜን ኮሪያ ለሙከራ የተተኮሱ ሚሳኤሎች የመምታት ሙከራ ያልተደረገባቸው ሲሆን ፒዮንግያንግ ለምን አሁን ይህ ስጋት እንደገባት አልገለጸችም።
ኣሜሪካ ቢ-52 የተሰኘውን ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በመጠቀም ከደቡብ ኮሪያ ጋር ወታደራዊ ልምምድ ልታካሂድ መሆኑን አስታውቃለች።
ለ10 ቀን በሚቆየው በዚህ ወታደራዊ ልምምድ ከሰሜን ኮሪያ ኑክሌር አረር ጦር ጥቃት ቢሰነዘር ምላሽ በሚሰጥበት ሁኔታ ላይ ያተኩራል ተብሏል።
አሜሪካ ደቡብ ኮሪያን ከማናቸውም ጥቃት ለመጠበቅ በገባችው ስምምነት መሰረት ከጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ ጥቃት እንዳይሰነዘር በተጠንቀቅ ላይ መሆኗን አስታውቃለች።
ለዚህም ሲባል ዋሽንግተን ከ28 ሺህ በላይ ወታደሮቿን ከሌሎች ዘመናዊ ከሆኑ የአየር እና ባህር ሀይል ጦር መሳሪያዎች ጋር በአካባቢው አሰማርታለች።