ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር የተፈራረመችውን የመከላከያ ስምምነት አጸደቀች
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ማስቀመጣቸው እና ሁለቱ ወገኖች የፈረሟቸውን ሰነዶች ከተቀያየሩ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል
ስምምነቱ ከሁለቱ በአንደኛቸው ላይ ጥቃት በሚደርስበት ወቅት አንዳቸው ሌላኛቸው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው
ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር የተፈራረመችውን የመከላከያ ስምምነት አጸደቀች።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ሐምሌ ወር የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን እና የሩሲያው ብላድሚር ፑቲን በፒዮንግያንግ የፈረሙትን የመከላከያ ስምምነት ማጽደቋን ሮይተርስ ኬሲኤንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ስምምነቱ ከሁለቱ በአንደኛቸው ላይ ጥቃት በሚደርስበት ወቅት አንዳቸው ሌላኛቸው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው።
ይህ ሪፖርት ይፋ የሆነው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ወታደራዊ ትብብር ላይ አለምአቀፋዊ ትችት በጨመረበት ወቅት ነው። ዩክሬን እና ምዕራባውያን ሀገራት ሰሜን ኮሪያ በዩክሬኑ ጦርነት ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ልካለች የሚል ክስ አቅርበዋል። ሩሲያ ይህን ክስ በቀጥታ አላስተባበለችም፤ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ግዛቷ ማስገባቷንም አላመነችም።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም በትናንትናው እለት በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ማስቀመጣቸው እና ሁለቱ ወገኖች የፈረሟቸውን ሰነዶች ከተቀያየሩ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን ዘገባው ጠቅሷል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንም ከሁለቱ አንዳቸው ጦርነት ካጋጠማቸው "ሁሉንም አማራጭ በመጠቀም ወታደራዊ እና ሌሎች ድጋፎች" ለማድረግ የሚያስችለው ስምምነት ህግ እንዲሆን ፈርመዋል።
ሴኡል፣ ዋሽንግተን እና ኪቭ ከ10ሺ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሩሲያ ውስጥ መግባታቸውን እየገለጹ ሲሆን የአሜሪካ ባለስልጣናት እና የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ የተወሰኑት በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ኩርስክ ግዛት ውጊያ እያካሄዱ ነው ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሀገራቸው ጦር ጋር ባደረጉት ውጊያ ጉዳት እንደደረሳቸው እና በሁለቱ መካከል የተካሄደው የመጀመሪያው ውጊያ በአለም አዲስ የአለመረጋጋት ምዕራብ እንደሚከፍት ባለፍው ሳምንት ተናግረዋል።