ኔታንያሁ ከማክሰኞው ምርጫ ወዲህ ከትራምፕ ጋር ሶስት ጊዜ መወያየታቸውን ገለጹ
ኢራን እና የምታስታጥቃቸው ሃይሎች እንቅስቃሴን ከአሜሪካው ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጋር በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑንም አስታውቀዋል
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ከ40 በላይ ንጹሃን ህይወት አልፏል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከባለፈው ማክሰኞ ወዲህ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ሶስት ጊዜ የስልክ ምክክር ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ከማክሰኞው ምርጫ ወዲህ “ኢራን እና ሁሉም የምታስታጥቃቸው ሃይሎች የደቀኑትን ስጋት በአንክሮ እየተከታተልን እየመከርንበት ነው” ሲሉም ነው የገለጹት።
የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ በነገው እለትም የዋይትሃውስ ቆይታቸውን እያጠናቀቁ ከሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ይመክራሉ ተብሏል።
የአሜሪካን ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም ያዛወሩት ትራምፕ ዳግም በተመረጡ ማግስት እስራኤል በሊባኖስ የጀመረችውን የምድር ውጊያ እና የአየር ጥቃት አጠናክራለች።
ከቤቱት በስተደቡብ 40 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው የአልማት ከተማ ትናንት በፈጸመችው የአየር ድብደባ ሰባት ህጻናትን ጨምሮ 23 ሰዎች መገደላቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኘው የጃባሊያ የስደተኞች ጣቢያ ከ40 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ፈጽማለች።
የእስራኤል ጦር ለሁለቱም ጥቃቶች የተለመደውን ምላሽ ሰጥቷል፤ ኢላማ የተደረጉት ስፍራዎች የሄዝቦላህ እና ሃማስ ታጣቂዎች ምሽጎችና የመሳሪያ ማከማቻዎች ነበሩ የሚል።
እስራኤል በሶሪያ መዲና ደማስቆ አቅራቢያ በፈጸመችው ጥቃት ደግሞ ሰባት ንጹሃን መገደላቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ሳና ዘግቧል።
በዚህ ጥቃት የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ኢላማ ተደርገው እንደነበር ተቀማጭነቱን ብሪታንያ ያደረገው የሶሪያውያን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ቢገልጽም የእስራኤል ጦር ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
እስራኤል በጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ በሚገባ እንዲገባ ካላደረገች የጦር መሳሪያ ድጋፍ ገደብ ሊደረግባት እንደሚችል በባይደን አስተዳደር የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል።
የትራምፕ መመረጥ ግን
የሰሜን ጋዛ ከተሞች ቤት ላሂያ እና ቤት ሃኑን በእስራኤል ጦር ከአንድ ወር በላይ ተከበው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተዘግቧል።
ቴል አቪቭ ሃማስ ዳግም እየተደራጀ ነው በሚልም በ13 ወሩ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ወዳስተናገደችው የጋዛ ከተማ ወታደሮቿን ዳግም መላኳ ነው የተነገረው።
በጋዛ፣ ሊባኖስ እና ሶሪያ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት እና የሰብአዊ ቀውስ መባባስ “በስልጣን ዘመኔ ጦርነት አልተቀሰቀሰም፤ የተጀመሩ ጦርነቶችንም አስቆማለሁ” ባሉት ዶናልድ ትራምፕ ዘንድ እንዴት ይታያል የሚለው ይጠበቃል።
ትራምፕ ከእስራኤል ጋር በእጅ አዙር እየተፋለመች በምትገኘው ኢራን ላይ ማዕቀቦችን ለመጣል መዘጋጀታቸውም እየተነገረ ነው።