ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ የዩክሬኑን ጦርነት እስከምታሸንፍ ድረስ እንደምትደግፋት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ
ሚኒስትሯ "ታሪካዊው እና ባህላዊው ግንኙነታችን ወደማይገበር ወታደራዊ ጓድነት አድጓል" ሲሉ ለላቭሮቭ ነግረዋቸዋል
ላቭሮቭ በሁለቱ ሀገራት ጦር መካከል ቅርብ ግንኙነት መኖሩን እና ይህም ወሳኝ የደህንነት ስራዎችን ለመከውን እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል
ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ የዩክሬኑን ጦርነት እስከምታሸንፍ ድረስ እንደምትደግፋት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።
ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ያለውን ጦርነት እስከምታሸንፍ ድረስ እንደምትደግፋት የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ሰን ሁይ በዛሬው እለት ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በሞስኮ ባደረጉት ውይይት ላይ ተናግረዋል።
"ታሪካዊው እና ባህላዊው ግንኙነታችን ወደማይገበር ወታደራዊ ጓድነት አድጓል" ሲሉ ቾይ ለላቭሮቭ ነግረዋቸዋል።
ቾይ እክለውም በፑቲን "ብልህ አመራር" የሩሲያ ጦር እና ህዝብ "የሉአላዊነት ዘመቻቸውን እና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ቅዱስ ትግል ድል ያደርጋሉ።"
"እኛም ድሉ እውን እስከሚሆንበት ቀን ድረስ ከሩሲያ ጓዶቻችን ጎን እንደምንቆም እናረጋግጣለን" ብለዋል ቾይ።
ላቭሮቭ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት ጦር መካከል ቅርብ ግንኙነት መኖሩን እና ይህም ወሳኝ የደህንነት ስራዎችን ለመከውን እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ላቭሮቭም ሆኑ ቾይ፣ አሜሪካ፣ ኔቶ እና ደቡብ ኮሪያ፣ በዚህ ሳምንት ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ 10ሺ ወታደሮችን ልካለች በማለት ያወጡትን መግለጫ አልጠቀሱም። የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ለእንደነዚህ አይነት መግጫዎች"ከዚህ በፊት ከተባለው በላይ የሚጨመር የለም" ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከእነዚህ ውስጥ 8ሺ የሚሆኑት ወታደሮች የዩክሬን ወታደሮች ባለፈው ነሐሴ ወር የሩሲያን ድንበር ጥሰው ወደገቡበት ኩርስክ ግዛት መድረሳቸውን በትናንትናው ገልጸዋል።
ላቭሮቭ "ምዕራባውን ኔቶን ወደ ምስራቅ ማስፋፋታቸውን እና ዘረኛው ሰርአት የሩሲያ የሆነን ሁሉ እንዲያጠፋ ማበረታታቸውን ተከትሎ የኮሪያ ወዳጆቻችን ለወሰዱት በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም ምስጋና እናቀርባለን" ብለዋል።
"በሁለቱ ሀገራት ጦር መካከል በጣም ቅርብ ግንኙነት ተፈጥሯል፤ ይህ ለእኛ እና ለእናንተ ደህንነት ወሳኝ የደህንነት ስራዎችን እንድንሰራ ያስችለናል።"
ቾይ የሁለቱ ሀገራት መሪወች ባለፈው ሰኔ ወር በፒዮንግያንግ የፈረሙትን ወታደራዊ ስምምነት የበለጠ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል። በስምምነቱ መሰረት ከሁለቱ በአንደኛቸው ላይ ጥቃት ቢከፈት አንደኛቸው ለሌላኛቸው ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።
በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ወታደሮቿን "ለልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ወደ ዩክሬን የላከችው ሞስኮ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ መሬት ላይ መኖራቸውን በቀጥታ አላረጋገጠችም፤ አላስተባበለችምም።
ቾይ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በሀገራቸው ላይ የኑክሌር ጥቃት ለመፈጸም እያሴሩ ነው ሲሉ ከሰዋል። በኮሪያ ባለህረ ሰላጤ ያለው ውጥረት በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ ይችላል ያሉት ቾይ ሰሜን ኮሪያ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ የኑክሌር የጦር መሳሪያዋን ማጠናከር እና ዝግጁ ማድረግ እንደማያስፈልጋት ለላቭሮቭ ነግረዋቸዋል።