የቫይረሱ ተጠርጣሪ ተገኝቶብኛል ያለችው ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ እንዲወሰድ ወስናለች
ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያ የኮሮና ተጠርጣሪ ማግኘቷን ሪፖርት አደረገች
በሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያ የኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪ መገኘቱን ሀገሪቱ አስታወቀች፡፡
መሪዋ ኪም ጆንግ ኡን ይህንን መነሻ በማድረግ የድንበር ከተማ በሆነችው ካኢሶንግ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል፡፡ በከተማዋ የመጀመሪያ የኮሮና ተጠርጣሪ ይፋ በመደረጉ ነው ከተማዋ ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው፡፡ ግለሰቡ ከደቡብ ኮሪያ እንደመጣ የተገለፀ ሲሆን በሕገ ወጥ መልኩ ድንበር ጥሶ እንደገባም ተዘግቧል፡፡ እንደ ሮይተርስ ዘገባ ኪም ጆንግ ኡን ይህንን ውሳኔ የወሰኑት የፖሊት ቢሮ ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡
በቫይረሱ የተጠረጠረው ግለሰብ ለሦስት ዓመታት ወደ ደቡብ ኮሪያ ኮብልሎ የነበረ ነው ተብሏል፡፡ የሰሜን ኮሪያው ኬሲኤንኤ በዘገባው ለግለሰቡ ምርመራ ይደረግ አይደረግ የገለጸው ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ያልተገመተ የህክምና ውጤት በተለይም በግለሰቡ ደም እና የመጸዳጃ ክፍል ላይ መታየቱ ነው የተነገረው፡፡ በመቀጠል ግለሰቡ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲሄድ ተደርጎ ከነማን ጋር ግንኙነት አለው የሚለው እየተጣራ ነው ተብሏል፡፡
አንድ የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ተንታኝ እንዳሉት በሀገሪቱ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ መደረጉ ሀገሪቱ ቫይረሱ መኖሩን እንድታምንና የንቃት ደወል እንዲሆናት ያደርጋል፡፡
በተለያዩ ማዕቀቦች የተጎዳው የሰሜን ኮሪያ ኢኮኖሚ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ከተስፋፋ የተባባሰ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል በዘገባው ተጠቁሟል፡፡ ሰሜን ኮሪያ የፒዮንግያንግ አጠቃላይ ሆስፒታልን በተያዘለት ጊዜ አጠናቃ ሳትገነባ ይህ ነገር መከሰቱ እውን ከሆነ ሁኔታዋን አስቸጋሪ ሊያደርጋ ይችላል ነው የተባለው፡፡
የኮሮና ቫይረስ ተጠረጠረ የተባለው ግለሰብ ከደቡብ ኮሪያ የመጣ ነው መባሉም እርዳታ ከጎረቤቷ ለማግኘጥ የምታደርገው ሙከራ አካል መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረው ይህ ግለሰብ እንደ ሰሜን ኮሪያ ያለ ከፍተኛ ትጥቅ ያለበትን ድንበር አንዴት ጥሶ እንደገባ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይሁንና ጦሩ ለዚህ ሃላፊነት እንዳለበትና ቅጣት ሊጠብቀው እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡