ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ አቅሟም ሆነ ፖለቲካዊ ተጽዕኖዋ አድጓል - ኪም ጆንግ ኡን
ሀገሪቱ ያልተጠበቁ ፈተናዎችን ባስተናገደችበት 2022 በምጣኔ ሃብት እና ባህል ዘርፍም እምርታን አሳይታለች ሲሉ ተደምጠዋል
ሰሜን ኮሪያ የ2023 እቅዷን ይፋ ታደርግበታለች ተብሎ የሚጠበቀው አመታዊ ስብሰባ እየተካሄደ ነው
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ አቅሟም ሆነ ፖለቲካዊ ተጽዕኖዋ አድጓል ብለዋል፡፡
መሪው ይህን ያሉት የሰሜን ኮሪያ ሰራተኞች ፓርቲ አመታዊ ስብሰባን በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ስብሰባውን በንግግር ሲከፍቱ የ2022 ዝርዝር አፈጻጸሞችን አንስተዋል።
ኪም ፒዮንግያንግ በፖለቲካ፣ መከላከያ፣ ምጣኔ ሃብትና ባህል ዘርፎች ተጽዕኖዋን ከፍ ያደረጉ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ግዙፍ ተግባራት የተከናወኑበት 2022 ያልተጠበቁ ፈተናዎችንም ያስተናገድንበት ነው ሲሉም ተደምጠዋል።የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ግን መሪው የጠቀሷቸውን ፈታኝ ጉዳዮች በዘገባው አላካተተም።
በ2022 ከ60 በላይ የባልስቲክ ሚሳይሎችን የሞከረችው ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቶቿ እና አሜሪካ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብታ ከርማለች።
በትናንትናው እለትም አምስት የሀገሪቱ ድሮኖች የደቡብ ኮሪያን ድንበር ጥሰው መግባታቸው ሴኡል ተዋጊ ጄቶቿን እና ሄሊኮፕተሮቿን እንድታሰማራ አስገድዷል።
ይሄው የፈረንጆቹ አመት ከጃፓን ጋር የሚሳይል ንግግር የጀመረችበት ነው።
አሜሪካ ከጎረቤቶቿ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር የምታደርገውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አጠናክራ መቀጠሏና ለሀገራቱ ኒዩክሌር እስከማስታጠቅ የደረስ ድጋፍ አደርጋለሁ ማለቷ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን አባብሶት ሰንብቷል።
ክብረወስን ሆኖ የተመዘገብ የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ በማዕቀብ አለንጋ እየተገረፈች ምጣኔ ሃብቷም ኪም ከጠቀሱት በተቃራኒው እየተዳከመ ስለመሆኑ ተንታኞች ያነሳሉ።
የኮሮና ወረርሽኝ እና የተፈጠሮ አደጋዎችም ለትንሿ ሀገር ዜጎች ፈተናውን አክብዶባቸዋል ነው የሚባለው።
የገዥው ሰራተኞች ፓርቲ አመታዊ ስብሰባ ላይ ግን ኪም ጆንግ ኡን በሰሜን ኮሪያውያን ዜጎች ላይ ስለተጋረጠው ችግር ያሉት ነገር የለም ወይንም በብሄራዊው ቴሌቪዥን ዘገባ ተቀንሷል።
ኪም በሪፖርታቸው በ2023 በብረት፣ ኬሚካል፣ ኤሌክትሪክ፣ ግንባታ እና ግብርና ዘርፎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ የ2023 እቅዷን ይፋ ታደርግበታለች ተብሎ የሚጠበቀው አመታዊ ስብሰባ ለቀናት ይቀጥላል ተብሏል።