ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ተኮሰች
ፒዮንግያንግ የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ የአየር ልምምድን በመቃወም ሁለት የባለስቲክ ሚሳይሎችን ተኩሳ አስጠንቅቃ ነበር
ከፈረንጆቹ 2017 በኋላ የሰሜን ኮሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ደቡብ ኮሪያ አየር ክልል ሲገቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል
የሰሜን ኮሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የደቡብ ኮሪያን አየር ክልል ከጣሱ በኋላ ሶኦል የማስጠንቀቂያ ተኩስ ተኩሳለች
የሰሜን ኮሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ደቡብ አየር ክልል ከገቡ በኋላ የደቡብ ኮሪያ ጦር የማስጠንቀቂያ ጥይቶችን መተኮሱን የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ገለጹ።
በርካታ የሰሜን ኮሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የኮሪያን ድንበር አቋርጠው በደቡብ ክልል ሰኞ ማለዳ ላይ መገኘታቸውን የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚንስቴር አስታውቋል።
የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል የሰሜን ኮሪያን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለመምታት ተዋጊ ጄቶችን ከማሰማራቱ እና ሄሊኮፕተሮች ከማጥቃታቸው በፊት የማስጠንቀቂያ ተኩሶችን መተኮሱን የመከላከያ ሚንስቴር አስታውቋል።
የፒዮንግያንግ ድሮኖች በጥይት ተመትተው እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
ከፈረንጆቹ 2017 በኋላ የሰሜን ኮሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ደቡብ ኮሪያ አየር ክልል ሲገቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
በወቅቱም የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ባለስልጣናት ሰው አልባ አውሮፕላኑ በደቡብ ኮሪያ የሚገኘውን የአሜሪካ የሚሳይል መከላከያ ስርዓት ፎቶ ግራፍ አንስቷል መባሉን ቲአርቲ ወርልድ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ የሰው አልባ አውሮፕላኖቿን ቁጥር ለመናገር ብታመነታም፤ የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ግን ፒዮንግያንግ 300 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አሏት ብላለች።
በፈረንጆቹ2014 በርካታ የተጠረጠሩ የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች ከድንበሩ በስተደቡብ ተገኝተዋል። በቴክኖሎጂ ረገድ ጉድለት አላቸው ቢባልም፤ ለደህንነት ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ግን ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ባለፈው አርብ ሰሜን ኮሪያ ሁለት የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳይሎችን ወደ ምስራቃዊ የውሃ ድንበር መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ ጥምር ጦር ኃላፊዎች አስታውቀዋል።
ሰሜን ኮሪያ እንደ ወረራ ልምምድ የምታየው የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ የአየር ልምምድ ተቃውሞ ተደርጎ ታይቷልም።
በቅርቡ ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያውን የስለላ ሳተላይት እና ተንቀሳቃሽ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ አድርጋለች።