ሰሜን ኮሪያ 600 መቶ ተጨማሪ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳን ሲኡል ገለጸች
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ረቡዕ እለት "የክብር ስጥታዎች" ናቸው ያለቻቸውን ቆሻሻ እና ጽዳጅ የያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፊኛዎችን መላኳን መግለጿ ይታወሳል
የደቡብ ኮሪያ ጦር ሁኔታውን ከመጀመሪያው ሲከታተለው እንደነበረ እና የአየር ቅኝት በማድረግ ፊኛዎችን መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል
ሰሜን ኮሪያ 600 መቶ ተጨማሪ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳን ሲኡል ገለጸች።
ሰሜን ኮሪያ 600 ተጨማሪ ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎችን በአንድ ሌሊት ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳን የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ይህ ሰሜን ኮሪያ ተቀናቃኟን ደቡብ ኮሪያን ለመተንኮስ የተጠቀመችበት የቅርብ ጊዜ ተግባርዋ ነው።
እንደ የተጨሰ ሲጋራ ቅሪት፣ ልብስ፣ ቆሻሻ ወረቀት እና ፕላስቲክ የመሳሰሉ ቆሻሻዎችን የያዙ ፊኛዎች ሌሊቱን የደቡብ ኮሪያን ድንበር አቋርጠው ማለፋቸውን የደቡብ ኮሪያ ኢታማዦር ሹም ተናግረዋል።
ኢታማዦር ሹሙ የደቡብ ኮሪያ ጦር ሁኔታውን ከመጀመሪያው ሲከታተለው እንደነበረ እና የአየር ቅኝት በማድረግ ፊኛዎችን መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ረቡዕ እለት "የክብር ስጥታዎች" ናቸው ያለቻቸውን ቆሻሻ እና ጽዳጅ የያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፊኛዎችን መላኳን መግለጿ ይታወሳል።
ሴኡል ይህን የሰሜን ኮሪያ ተግባር አደገኛ እና ንቀት የተሞላበት ነው ስትል በንዴት መልስ ሰጥታለች።
የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ሺን ዎን ሲክ በሻንግሪ ላ በተደረገው የጸጥታ ውይይት ጎንለጎን ከአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ልዮድ ኦስቲን ጋር ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት የፊኛዎቹ መላክ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የሚጥሱ ብለዋል። ኦስቲን እና ሺን ዎን ሲክ በደቡብ ኮሪያ- አሜሪካ ስምምነት መሰረት ሰሜን ኮሪያ ለምትፈጽማቸው ትንኮሳዎች የተቀናጀ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስማምተዋል።
በሰሜን ጂዎንግሳንግ፣ በጋንግዎን ግዛት እና በተወሰኑ የሲኦል ከተማ ክፍሎች ሰዎችን እነዚህን ፊኛዎችን እንዳይነኳቸው ማስጠንቀቂያ ተላልፎ ነበር።
የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የጸጥታ ኮሚቴ ወደ ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ድምጽ ያላቸው ላውድስፒከሮችን መልቀቅ ስለመጀመር ጉዳይ በዛሬው እለት እንደሚመክር ሮይተርስ ዮንሃብ የተባለውን የዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
ደቡብ ኮሪያ እንዲህ አይነቱን ተግባር በ2018 ያቆመችው ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ከተደረገ ያልተጠበቀ ስብሰባ በኋላ ነበር።