ሰሜን ኮርያ በፊኛዎች ወደ ደቡብ ኮሪያ ቆሻሻ ላከች
ከትናንት ጀምሮ 150 “አስቀያሚ” ቆሻሻዎችን የያዙ ፊኛዎች በደቡብ ኮርያ የድንበር ከተሞች ላይ አርፈዋል
ደቡብ ኮሪያም ከዚህ ቀደም በፊኛዎች ሙዚቃ፣ ፊልሞች እና 300ሺ በራሪ ወረቀቶችን ወደ ሰሜን ኮሪያ መልኳ ይታወሳል
ሰሜን ኮርያ በፊኛዎች ወደ ደቡብ ኮሪያ ቆሻሻ ላከች።
በሁለት የደቡብ ኮሪያ የድንበር ከተሞች ላይ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ መታየት የጀመሩት ፊኛዎች በውስጣቸው ‘’አስቀያሚ’’ የተባሉ ቆሻሻዎችን እና የፕሮፖጋንዳ በራሪ ወረቀቶችን የያዙ ናቸው፡፡
ሁለቱ ሀገራት ከ1950ው የኮሪያ ጦርነት በኋላ ፊኛዎችን ለፕሮፖጋንዳ አላማ ይጠቀማሉ፡፡ ሰሜን ኮሪያ ድርጊቱን የፈጸመችው ከሰሞኑ የደቡብ ኮሪያ አንቂዎች የፒዮንግያንግን መንግስት የሚያጥላሉ በራሪ ወረቀቶችን ማሰራጨታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የሰሜን ኮሪያን ቆሻሻዎች የያዙት ፊኛዎች ከትናንት ምሽት ጀምሮ በደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴኡል ሰሜናዊ አቅጣጫ በሚገኙ ግዛቶች መታየታቸው ተዘግቧል።
ይህን ተከትሎም ዜጎች በቤታቸው እንዲቀመጡ የጽሁፍ መልዕክት በስልኮቻቸው ተልኮላቸዋል ነው የተባለው።
ፊኛዎቹ የተሸከሟቸው ፌስታሎች ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ የመጸዳጃ ቤት ወረቀቶች (ሶፍቶች) እና ሌሎች ምንነታቸው ያልተለዩ ቆሻሻዎችን በውስጣቸው መያዛቸውንም የሴኡል ባለስልጣናት መናገራቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
= የደቡብ ኮሪያ ጦር ድርጊቱን የአለም አቀፍ ህግን የጣሰ የዜጎችንም ህይወት አደጋ ላይ የጣለ ሲል አውግዞታል፡፡
የሀገሪቱ ጦር ቆሻሻዎቹ መርዛማነት ሊኖራቸው ስለሚችል ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ የደቡብ ኮሪያ የማህበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) በሰሜን ኮሪያ የተከለከሉ የደቡብ ኮርያ ታዋቂ የፖፕ ሙዚቃዎችና ቪዲዮዎችን፣ ፊልሞችና ድራማዎች፣ገንዘብ እና ቸኮሌት እንዲሁም ከ300ሺህ በላይ የፕሮፖጋንዳ ወረቀቶች ጋር በተመሳሳይ ወደ ሰሜን ኮሪያ ልከው ነበር፡፡
በሰሜን ኮሪያ ከውጭ የሚገቡ የትኛውንም አይነት እቃዎች ይዞ መገኝት ከባድ ቅጣትን የሚያስከትል ነው፡፡ ኢንተርኔት እና ነጻ ሚድያ በሌለባት ሀገር ዜጎች የውጭው አለም ስለሚገኝበት ሁኔታ ምን አይነት መረጃ የላቸውም፡፡
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪምጆንግ ኡንን የሚያወድሰውን በቅርቡ የተለቀቀውን ሙዚቃ ሲሰማ የተገኘን ሰው እቀጣለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።