የሰሜን ኮሪያ የስለላ ሳተላይት “ዋና ዋና ኢላማዎችን” ፎቶ አንስታ መላክ ጀመረች
ሳተላይቷ የዋይትሃውስ እና የፔንታጎንን ጨምሮ የጎረቤት ደቡብ ኮሪያን መዲና ምስሎች መላኳ ተገልጿል
ሴኡል ምስሎቹ በይፋ ስላልተለቀቁ የስለላ ሳተላይቷን አቅም መገምገም ይከብዳል ብላለች
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ያመጠቀቻት የስለላ ሳተላይት ምስሎችን መላክ መጀምሯ ተነግሯል።
የስለላ ሳተላይቷ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መቀመጫ ዋይትሃውስን እና የመከላከያ ሚኒስቴሩን ቢሮ (ፔንታጎን) የሚያሳዩ ምስሎች መላኳ ነው የተገለጸው።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡንም ምስሎቹን መመልከታቸውን የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ (ኬሲኤንኤ) ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቃኘት ታገለግላለች የተባለች የስለላ ሳተላይት ባለፈው ሳምንት በተሳካ ሁኔታ ማስወንጨፏ ይታወሳል።
ሳተላይቷ “ወሳኝ የኢላማ ክልሎች”ን ምስል እየላከች ነው ያለው ኬሲኤንኤ፥ የደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል እና የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎችን ምስል መላኳንም አመላክቷል።
ኪም ጆንግ ኡን በአሜሪካ የሚገኘውን የአንደርሰን አየር ሃይል ጣቢያ እና ኖርፎልክ በተሰኘው አካባቢ የሚገኘውን የአሜሪካ ባህር ሃይል እንቅስቃሴ የሚያሳዩ በሳተላይቷ የተላኩ ምስሎች መመልከታቸው ተገልጿል።
በእነዚህ ወታደራዊ ጣቢያዎች አሜሪካ አራት በኒዩክሌር የሚሰሩ ግዙፍ መርከቦችን ጨምሮ በርካታ የጦር መሳሪያዎች ማከማቸቷንም ነው የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዥን ጣቢያ የዘገበው።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ሰሜን ኮሪያ ለሶስተኛ ጊዜ ያደረገችውን የስለላ ሳተላይት ሙከራ የመንግስታቱ ድርጅትን ክልከላ ይቃረናል በሚል መቃወማቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ፒዮንግያንግ ግን አሳሳቢ የሆነውን የዋሽንግተን እና ሴኡል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቃኘት ሳተላይቷ ወሳኝ ድርሻ እንዳላት ስትገልጽ ቆይታለች።
አሜሪካ ስለሳተላይቷ ምስሎች እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጠችም።
ደቡብ ኮሪያ ግን በሳተላይቷ ተነሱ የተባሉት ምስሎች በይፋ ስላልተለቀቁ የስለላ ሳተላይቷን አቅም ለመገምገም አዳጋች ነው ብላለች።