ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ድሮኖችን ስጦታ ሰጠች
ኪም ጆንግ ኡን ለ6 ቀናት በሩሲያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው
ኪም ጆንግ ኡን እና ፕሬዝዳንት ፑቲን አርስ በእርስ የሽጉጥና ክላሽ ስጦታ ተሰጣጥተዋል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ በነበራቸው ጉብኝት ድሮኖችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በስጦታ እንደተሰጣቸው ተገለፀ።
ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ ለስድስት ቀናት በሩሲያ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በትናንትናው እለት ከሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ ጋር በቫልዲቮስቶክ ተገናኝተዋል።
በተገናኙበት ጊዜም የጦር ኤግዚቢሽን በጋራ የጎበኙ ሲሆን፤ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ተመልክተዋል።
በዚሁ ወቀትም ኪም ጆንግ ኡን፤ አምስት ካሚካዜ ድሮኖች፣ እና ያለ መንደርደር ቀጥታ ወደላይ የሚነሳ ጌራን 25 የተባለ ድሮን በስጦታ እንደሰጣቸው ታስ ዘግቧል።
በተጨማሪም የሩሲያ ፕሮሞርዬ ግዛት አስተዳዳሪ ለኪም ጆንግ ኡን ጥይት የማይበሳቸው በርካታ ጃኬቶችን እንዲሁም በጦር እና በሌሎች ካሜራዎች እይታ ውስጥ የማይገባ ልዩ ልብስ ሶጦታ ሰጥተዋቸዋል ነው የተባለው።
ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ ከፑቲን ጋር በተገናኙበት ጊዜ አርስ በእርስ የሽጉጥና ክላሽ ስጦታ ተሰጣጥተዋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በዛሬው እለት በሩሲያ ያደረጉትን የ6 ቀናት ጉብኝት አጠናቀው በመጡበት ጥይት በማይበሳው ባቡር ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።