ሰሜን ኮሪያ ሁለት የኒውክሌር ተሸካሚ ክሩዝ ሚሳኤሎችን መሞከሯን አስታወቀች
የክሩዝ ሚሳኤሎች ሙከራው የውጊያ ላይ ጥንካሬን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ሰሜን ኮሪያ አስታውቃለች
ሁለቱ ሚሳዔሎች 2 ሺህ ኪሎ ሜትር በመጓዝ ኢላማቸውን መትተዋል ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ ሁለት የረጅም ርቀት የኒውክሌር አረር ተሸካሚ የክሩዝ ሚሳዔሎችን በትናትናው እለት መሞከሯን አስታውቃለች።
የሚሳዔል ሙከራው በትናንትናው እለት የተካሄደ ሲሆን፤ ሙከራው የሰሜን ኮሪያን የውጊያ ላይ ጥንካሬ እና ቅልጥፍናን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን የሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሆነው ኬ.ሲ.ኤን.ኤ ዘግቧል።
ፒንግያንግ ትናንት ያደረገችው የሚሳዔል ሙከራ ከሰሞኑ ስታካሂደው የነበረው ተከታታይ የሚሳዔል ሙከራዎች መካከል ሲሆን፤ ይህም ሀገሪቱ ከ5 ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ሙከራ ልታደርግ ትችላልች በሚል በኮሪያ ልሳነ ምድር ስጋትን አጭሯል።
ሰሜን ኮሪያ በትናንትናው እለት ያስወነጨፈችው ክሩዝ ሚሳዔሎች በባህር ላይ 2000 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ የተቀመጠላቸውን ኢላማ መምታት መቻላቸውን የኬ.ሲ.ኤን.ኤ ዘገባ ያመለክታል።
የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሙከራውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት፤ “የሀገሪቱን የታክቲካል የኒውክሌር ጥቃት አቅም የሚያሳይ የተሳካ ሙከራ ነው” ሲሉ አድንቀዋል።
“የክሩዝ ሚሳዔል ሙከራዎቹ ለጠላቶቻችን ሌላ ማስጠነቀቂያ ነው” ያሉት ኪም ጆንግ ኡን፤ ሀገራቸው ስትራቴጂካዊ ኒውክሌር አቅሟን የማሳደገ ስራዋን ትቀጥላች ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራዎችን እያደረገች እንደሆን ይታወቃል።
ሰሜን ኮሪያ እንዳስታወቀችው የሰሞኑ የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራዎች አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ላካሄዱት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የአፀፋ ምላሽ ለመስጠት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቃለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ በሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ በጃፓን የአየር ከልል ላይ አደገኛ የሆነ የሚሳዔል ማስወንጨፍ ማካሄዷን ተከተሎ አስቸኳይ ስበስባ ጠርቶ ነበረ።
የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማእቀቦች እንዲጣሉ ምክረ ሀሰብ ቢቀርብም ሩሲያ እና ቻይና ሀሳቡን ውድቅ አድርገዋል።
በዚህ የተበሳጨችው አሜሪካ፤ ቻይና እና ሩሲያ ማእቀቦችን በመቃወም ለሰሜን ኮሪያ ከለላ እየሰጡ ነው ስትል ወቀሳ አቅርባለች።