መሪው ኃያል ሀገር ለመገንባት ለያዙት ታላቅ ግብ ሀገራቱ በቅርበት እንዲተባበሩ ጥሪ አድርገዋል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር "እጅ ለእጅ" ለመያያዝ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ኪም ሁለቱ መሪዎች ኃያላን ሀገር ለመገንባት ያላቸውን የጋራ ዓላማ በስልታዊ ትብብር ለማጠናከር ቃል መግባታቸውን የሰሜን ኮሪያ የመንግስት መገናኛ ብዙኸን የሆነው ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
ኪም ጆንግ ኡን የሩስያ ብሄራዊ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለፑቲን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዩክሬንን ለመውረር ያደረጉትን ውሳኔ ትክክለኛነት አድንቀዋል።
የፒዮንግያንግ መሪ ለሞስኮ “ሙሉ ድጋፍ እና አጋርነት” እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
"ፍትህ እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነኝ። እናም የሩሲያ ህዝብ ለድል ክብር መስጠቱን ይቀጥላል" ሲሉ ኪም በመልዕክታቸው ተናግረዋል።
ኪም ከሞስኮ ጋር “የቅርብ ስልታዊ ትብብር” ለማድግ ጥሪ አቅርበዋል።
“ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ ፍላጎት የሆነውን ኃያል ሀገር የመገንባት ታላቅ ግብ ለማሳካት በቅርበት እንተባበር” ሲሉም ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ዓመት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ሞስኮን ደግፋ ከክሬምሊን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ሞክራለች።
ለዚህ እርምጃዋ የአሜሪካን እና የምዕራባውያንን ፖሊሲና ጣልቃ-ገብነትን ተጠያቂ አድርጋለች።