ሰሜን ኮሪያ አዲስ የባሊስቲክ ሚሳኤል ማልማት ላይ ትኩረት እንደምታደርግ ገልጻለች
ሰሜን ኮሪያ አዲስ ወታደራዊ አዛዥ ሾመች፡፡
ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ እና ከምዕራባዊያን ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ ያለችው ሰሜን ኮሪያ አዲስ ወታደራዊ አዛዥ መሾሟ ተገልጿል፡፡
እንደ ደቡብ ኮሪያው የዜና አገልግሎት ዘገባ ከሆነ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኪም ጆን ኡን ወታደራዊ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ አመራሮችን ሹም ሽር አድርገዋል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ሰራተኞች ፓርቲ ዋና ጸሃፊ እና የማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን የነበሩት ፓርክ ጁንግ ቹን ከስልጣን ተነስተዋል፡፡
በአዲሱ የሹም ሽር መሰረት የቀድሞው የሰሜን ኮሪያ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ሪ ዮንግ ጊል የሀገሪቱ ሰራተኞች ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ሆነው ተሸመዋል፡፡
ካንግ ሱን ናም ደግሞ የሰሜን ኮሪያ መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ፓርክ ሱ ኢል ደግሞ የማህበራዊ ደህንነት ሚኒስትር ሆነው እንደተሸሙ ተገልጿል፡፡
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በየጊዜው የካቢኔያቸውን ስልጣን ሽግሽግ የሚያደርጉ ሲሆን ወታደራዊ ደህንነታቸውን እና ስልጣናቸውን ማስጠበቅ የሹመታቸው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዝዳንት ኪም ሀገራቸው ከአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ሊደርስባቸው የሚችለውን የሚሳኤል ጥቃት ለመመከት አዲስ ባሊስቲክ ሚሳኤል እንዲለማ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በተለይም በተጠናቀቀው የ2022 ዓመት መጠነ ሰፊ የረጅም ርቀት ተጓዥ ሚሳኤል ሙከራ ስታደርግ የቆየች ሲሆን የዓመቱ የመጨረሻ ቀንን ወደ ኮሪያ ባህረሰላጤ ሚሳኤል በመተኮስ አጠናቃለች፡፡
የኮሪያ ባህረ ሰላጤ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ የወደቀ ሲሆን በተለይም ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ስጋት እንደገባቸው በይፋ በመናገር ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ ሀገራት ከሰሜን ኮሪያ ሊሰነዘር የሚችል ጥቃት ሊኖር ይችላል በሚል የአየር እና ባህር ላይ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በተደጋጋሚ አድርገዋል፡፡