ሰሜን ኮሪያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዚህ ዓመት ብዙ ሚሳይሎችን አስወንጭፋለች
ሰሜን ኮሪያ ከኮሪያ ልሳነ ምድር በስተምስራቅ በኩል ሶስት የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳይሎችን ወደ ባህር መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታውቋል።
ይህ እርምጃ የመጣው ሰሜን ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2017 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ ደቡብ ኮሪያ አየር ክልል ካስገባች ከአምስት ቀናት በኋላ ነው።
ሰሜን ኮሪያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዚህ ዓመት ብዙ ሚሳይሎችን አስወንጭፋለች።
ዋሽንግተን የቅርብ ጊዜው የሚሳይል ማስወንጨፍ ለአሜሪካም ሆነ ለአጋሮቿ አስቸኳይ ስጋት እንደማይፈጥር ተናግራለች።
ሶስቱ የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤሎች የተተኮሱት ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በስተደቡብ ከምትገኘው ኸዋንጋይ ግዛት ነው ሲሉ የደቡብ ኮሪያ የጦር መኮንኖች ተናግረዋል።
አክለውም “የሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፍ በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ እንዲሁም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላምና መረጋጋትን የሚጎዳ ከባድ ቅስቀሳ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ሚሳይሎቹ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደበረሩም የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታውቋል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር በዚህ ሳምንት ሰሜን ኮሪያ የጋራ ድንበራቸውን አቋርጣ የላከቻቸው አምስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መምታት ባለመቻሉ ይቅርታ ጠይቋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሴኡል የማስጠንቀቂያ ተኩስ በመተኮስ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን ለመምታት ጄቶች እና ሄሊኮፕተሮች ልካለች።
በቅርቡ አሜሪካ እና የእስያ አጋሮቿ ሰሜን ኮሪያ ከጀመረችው የሚሳይል ሙከራ ጋር በተገናኘ በሦስት የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዮል ወግ አጥባቂ መንግስት በግንቦት ወር ስልጣን ከያዘ በኋላ በፒዮንግያንግ ላይ የበለጠ ጠንካራ አቋም በመያዝ በሰሜን እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነት ተባብሷል ተብሏል።