ግድያ የበዛባት አሜሪካ አዲስ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ አውጥታለች
በአሜሪካ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች በጦር መሳሪያ እንደተገደሉ ተገለፀ።
በአሜሪካ እድሜው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሖነ ሰው ሁሉ የጦር መሳሪያ እንደ ሌሎች ሸቀጦች ከገበያ ስፍራዎች መሸመት ይችላል።
ይሄንን ተከትሎም በርካታ አሜሪካኖች በየቤታቸው የጦር መሳሪያ ያላቸው ሲሆን የእርስ በርስ ግድያ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ በየጊዜው የአሜሪካ ፖለቲከኞችን ሲያጨቃጭቅ የቆየ ሲሆን ግድያች መጨመራቸውን ተከትሎ አዲስ ህግ ተዘጋጅቷል።
የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት አዲሱን ለጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ እውቅና የሰጠ ሲሆን በቀጣይ በሚደረጉ የሕግ አውጪዎች እንደሚያጸድቁት ይጠበቃል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ ህግ ከጸደቀ አሜሪካ የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን በሚመለከት ከወጡ ህጎች መካከል ከ30 ዓመት በኋላ ወሳኝ ህግ ይሆናል ተብሏል።
ዲሞክራቶች በዋናነት የህ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ እንዲወጣ የሚፈልጉ ሲሆን 15 የሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮችም ህጉን ደግፈዋል ተብሏል።
በአሜሪካ በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ውስጥ ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች በጦር መሳሪያ የተገደሉ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ በኒዮርክ አንድ ሰው 31 ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል።
የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህጉ ፖሊስ የጠረጠራቸውን የጦር መሳሪያ ባለቤቶች ላይ ምርምራ እና ሌሎች እርምጃዎችን እንዲወስድ ከመፍቀዱ ባለፈ ሰዎች ጦር መሳሪያ ግዢ ከመፈጸማቸው በፊት የአእምሮ ጤናቸውን ጨምሮ እድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ መሆኑን እንዲፈትሽ ይፈቅዳል ተብሏል።
ይሄንን ህግ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት እና ግለሰቦች የተቀበሉት ሲሆን በጦር መሳሪያ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ግን ህጉን ተቃውመዋል።
የአሜሪካ ብሄራዊ ጥይት አምራቾች ማህበር ህጉ በጦር መሳሪያ የሚፈጸሙ ግድያዎችን አያስቆምም በሚል ተቃውሟል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህጉ በሚፈለገው መንገድ እየሄደ መሆኑን ገልጸው አሁንም ቀሪ ስራዎች ይቀራሉ ብለዋል።
በዓለማችን በመኖሪያ ቤቶች ከሚመዘገቡ ሞቶች መካከል የጦር መሳሪያ ግድያ ቀዳሚው ሲሆን በአሜሪካ ከሚመዘገቡ ሞቶች ውስጥ 79 በመቶ በጦር መሳሪያ የሚፈጸም ነው።
አሜሪካ፣ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና እንግሊዝ በጦር መሳሪያ ግድያ የሚፈጸምባቸው ሀገራት እንደሆኑ የካናዳ ጥናት ማዕከል 2020 ሪፖርት ያስረዳል።