የሰሜን ኮሪያን ሁለተኛ የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ የተወነጨፈችው ሮኬት ፈነዳች
ፒዮንግያንግ ሙከራውን ያደረገችው ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በሴኡል የሶስትዮሽ ምክክር ማድረግ በጀመሩበት ወቅት ነው
ሰሜን ኮሪያ አጋሯ ቤጂንግም የፈረመችበትን የሶስቱ ሀገራት መግለጫ ተቃውማለች
ሰሜን ኮሪያ ሁለተኛ የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱ ተነገረ።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኪሲኤንኤ) እንደዘገበው ሳተላይቷ የመጠቀችባት ሮኬት ከጥቂት ቆይታ በኋላ ፈንድታለች።
ሮኬቷ የፈነዳችው ከሞተር ችግር ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም የሀገሪቱን ኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር መናገራቸውን አስነብቧል።
ፒዮንግያንግ ያልተሳካውን የሳተላይት ማስወንጨፍ ሙከራ ያደረገችው ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና እና ጃፓን ከአራት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴኡል የሶስትዮሽ ምክክር ማድረግ በጀመሩበት እለት ነው።
ሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የኢኮኖሚ አጋሯ ቻይና በቀጠናው ጉዳይ ከጎረቤቶቿ ጋር ስትመክር መሰል ጸብ አጫሪ ድርጊት ስትፈጽም የትናንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ፣ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ እና የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ከጋራ ስብሰባቸው በኋላ ሰሜን ኮሪያ የሳተላይት ሙከራዋን እንድታቆም የሚያሳስብ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር በንግግራቸው የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት በፖለቲካዊ ንግግር ሊፈታ ይገባዋል ከማለት ውጪ የፒዮንግያንግን የሳተላይት ሙከራ አላነሱም ተብሏል።
ይሁን እንጂ ሰሜን ኮሪያ ለጃፓን ከህዳር 19 ጀምሮ ባሉት ሰባት ቀናት ሳተላይት እንደምታስወነጭፍ አስታውቃ በትናንትናው እለት ሙከራውን ማድረጓ በቤጂንግ ተሳትፎ መበሳጨቷን እንደሚያሳይ ነው የተነገረው።
ከሩሲያ እና ቻይና ጋር በመተባበር በምዕራባውያን ላይ የሚቃጣን “አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት” መመከት ላይ ያተኮሩት ኪም ጆንግ ኡን የቤጂንግ ከሴኡል እና ቶኪዮ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በበጎ አይመለከቱትም።
አሜሪካ የጸጥታው ምክርቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንዳይጥል ከሞስኮ ጋር ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን በመጠቀም ለፒዮንግያንግ አጋርነቷን ያሳየችው ቤጂንግ የኪም ጆንግ ኡንን “አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነት” እቅድ በግልጽ ስትደግፍ አትታይም።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ፊርማቸው ያረፈበትን የሶስትዮሽ የጋራ መግለጫ በጥብቅ ተቃውሟል።
ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓንን “በውጥ ጉዳያችን አትግቡ” ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ ግን ቻይናን አልወቀሰም።
ሰሜን ኮሪያ በ2024 ሶስት የስለላ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ ያቀደች ሲሆን፥ የመጀመሪያውን ሳተላይት ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ህዳር ወር ላይ በተሳካ ሁኔታ ማምጠቋ ይታወሳል።