“ሰሜን ኮሪያ በሙዚቃ የስነልቦና ጦርነት አውጃብኛለች” - ደቡብ ኮሪያ
ሴኡል በቲክቶክ በርካቶች እየተቀባበሉት ያለውን ኪም ጆንግ ኡንን የሚያወድስ ሙዚቃ እንዳይታይ ወስናለች
“ፍሬንድሊ ፋዘር” የሚል ርዕስ ያለው ሙዚቃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል
ደቡብ ኮሪያ ለጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የተቀንቀነውንና በቲክቶክ ተወዳጅነትን ያተረፈውን ሙዚቃ በሀገሪቱ እንዳይታይ ልታግድ ነው።
የሀገሪቱ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተቋም በሚያዚያ ወር የተለቀቀው ሙዚቃ የሴኡልን የብሄራዊ ደህንነት ህግ የሚቃረን ነው ብሏል።
የደህንነት ህጉ የሰሜን ኮሪያን ድረገጾች እና መገናኛ ብዙሃን መመልከት የሚያግድ ሲሆን፥ የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደርን የሚደግፍ ንግግር ማድረግና ይህንኑ የሚያንጽባርቅ ባህሪ ማሳየትም እንደሚያስቀጣ ያስቀምጣል።
የብሄራዊ ደህንነት ህጉን ተላልፈው የሚገኙ አካላት እስከ ሰባት አመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጡ ቢቀመጥም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅጣቱ እየላላ መሄዱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ሴኡል የመናገርና የመረጃ ነጻነትን ይጋፋል የተባለውን ህግ በመጥቀስ ዜጎቿ የፒዮንግያንግን አዲስ ሙዚቃ እንዳያደምጡ አሳስባለች።
“ሙዚቃው ኪም ጆንግ ኡንን የሚያሞግስና የሚያንቆለጻጽስ ነው” ያለው የደቡብ ኮሪያ የኮሚዩኒኬሽን ስታንዳርድ ኮሚሽን፥ በቲክቶክ በሚሊየኖች የታየው ሙዚቃ በሴኡል እንዳይታይ መወሰኑን አስታውቋል።
“ፍሬንድሊ ፋዘር” የሚል ርዕስ ያለው ሙዚቃ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት በደቡብ ኮሪያ ላይ የከፈቱት የስነልቦና ጦርነት አካል መሆኑንም ነው ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ የጠቆመው።
ኪም ጆንግ ኡንን “ታላቁ አባታችን” እያለ የሚያሞግሰው ዘፈን ከ29 በላይ ቪዲዮዎች ተሰርተውለት በቲክቶክ አለምን ማዳረሱ ያሳሰባት ሴኡል ቪዲዮዎቹ እንዴት እንዳይታዩ ማገድ እንደምትችል በዝርዝር አልገለጸችም ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
የሙዚቃው ስልተምት የስፔን እና ፈረንሳይ የፖፕ ሙዚቃን ያስታውሳል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም ፒዮንግያንግ ከኒዩክሌር ባሻገር በሙዚቃውም አለም ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንደምትችል ያሳየችበት መሆኑን ይገልጻሉ።
በተለያየ የስራ መስክ የተሰማሩ ሰሜን ኮሪያውያን መሪያቸውን በሚያወድሰው ሙዚቃ የሰሯቸው የቲክቶክ ቪዲዮዎች ለሚሊየኖች ተደራሽ መሆናቸው ተዘግቧል።
የ1953ቱ የኮሪያ ጦርነት በተኩስ አቁም ሁለት ኮሪያዎችን ቢፈጥርም ሀገራቱ እስካሁን የሰላም ስምምነት አለመፈራረማቸውን ተከትሎ በጦርነት ውስጥ እንዳሉ ይቆጠራል።
@dprksongs #北朝鮮 #親しき父 #친근한어버이 #DPRK ♬ オリジナル楽曲 - dprksongs