የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን ወደ ሰሜን ኮሪያ ሊያቀኑ ነው
ፕሬዝደንቱ ለአዲስ የስልጣን ዘመን ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ በቻይና እና ቤላሩስ ጉብኝት አድርገዋል
አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ እና ሩስያ በመጪው ምርጫ ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ በሚል ሰግታለች
ከጆሴቭ ስታሊን ቀጥሎ በሩስያ መንበር ላይ ለረጅም ግዜ የቆዩት የሩሳያው ፕሬዝዳንት በአዲሱ የስልጣን ዘመናቸው ወዳጅ ወዳሏቸው ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡
ቃለ መሀላ ከፈጹሙ በኋላ ለመጀመር ግዜ ወደ ቻይና ያቀኑት ፑቲን ከሰሞኑ በቤላሩስ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ቀጣይ ማረፊያቸው ደግሞ ሰሜን ኮሪያ እንደሆነች እየተነገረ ነው፡፡
ጉዞው መቼ እንደሚደረግ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር የተቆጠቡት የክሪምሊን ቃል አቀባይ ዲሚተሪ ፔስኮቭ በቅርቡ ፕሬዝዳንቱ ወደ ፒንግያንግ ያቀናሉ ብለዋል፡፡
በተያዘው የፈንረጆቹ አመት መጀመርያ ለፑቲን ይፋዊ የጉብኝት ግብዣ ያቀረበችው ሰሜን ኮሪያ ‘’የቅርብ ወዳጄ’’ ናቸው ያለቻቸውን ፕሬዝዳንት በሞቀ አቀባበል እንደምትቀበል አስታውቃለች፡፡
ቃል አቀባዩ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ‘’እንደሚታወቀው ከሰሜን ኮሪያ የቀረበውን ይፋዊ የጉብኝት ጥያቄ ተከትሎ የጉዞ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ግዜው ሲደርስ ቀኑን ይፋ እናደርጋለን’’ ብለዋል፡፡
ከአሜሪካ ጋር ውጥረት ውስጥ የሚገኙት ሀገራት ሁለትዮሽ ግንኙነት የዩክሬን ጦርነት መጀመርን ተከትሎ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ባለፈው አመት መስከረም ወር ላይ በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ክፍል ጉብኝት ያደረጉት የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከመከሩ በኋላ ሁለት ሩሲያ ሰራሽ ኦውሩስ ሊሞዚኖች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
አሜሪካ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት እንደትልቅ ስጋት የምትመለከተው ጉዳይ ነው። ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች ደግሞ ሀገራቱ በ2024ቱ ምርጫ ላይ ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋትን የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡
በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያ ጣልቃ ገብነት ስጋት
የነጩ ቤተ መንግስት ሃላፊዎች የፒንግያንግ እና ሞስኮ መቀራረብ በ2024ቱ ምርጫ ላይ ጣልቃ ገብነትን ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶችን በማባባስ የሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሽፉ ሊያግዙ ይችላሉ በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡
ኤንቢሲ ኒውስ የአሜሪካ የደህንት ተቋማትን ጠቅሶ እንደዘገበው ኪም ጆንግ ኡን የህዳሩ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት “የኦክተበሩ ሰርፕራይዝ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጠብ አጫሪ ወታደራዊ እንቅሰቃሴዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
ኒውክሌር መሸከም የሚችሉ የባላስቲክ ሚሳይሎች ሙከራን ያካትታል የተባለው እንቅስቃሴ ከሀማስ እና እስራኤል ጦርነት እንዲሁም ከዩክሬን እና ሩስያ ውግያ ሌላ ቀውስ አለም ላይ ሊመጣ ነው በሚል አሜሪካዊያን መራጮች የመሪ ለውጥ እንደሚያስፈልግ እንዲያምኑ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ውስጥ ፑቲን ለሰሜን ኮሪያ ዋነኛ አጋር እንደሚሆኑ የደህንነት መረጃዎቹ ትንታኔ ጠቁመዋል፡፡ በ2016ቱ ምርጫ ጣልቃገብነት ስትከሰስ የነበረችው ሞስኮ በዚህኛውም ምርጫ ላይ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ወደ ስልጣን ለመመለስ ሚና ሊኖራት ይችላል ተብሏል።