ፒዮንግያንግ በታህሳስ ወር ሙከራዋ ተሳክቷል የተባለችውን ሳተላይት በዚህ ወር መጨረሻ እንደምታመጥቅ ይጠበቃል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገራቸው የመጀመሪያዋ የስለላ ሳተላይት በተያዘላት መርሃግብር እንድትመጥቅ አሳስበዋል።
ኪም ጆንግ ኡን በትናንትናው እለት የሀገሪቱን የስፔስ ኤጀንሲ ጎብኝተዋል።
መሪው በዚሁ ወቅትም ከአሜሪካ እና ከጎረቤት ደቡብ ኮሪያ የተደቀነብንን አደጋ ለመመከት ሳተላይቷ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት አለባት ማለታቸውን ነው የሀገሪቱ የቴሌቪዥን (ኬሲኤንኤ) የዘገበው።
ፒዮንግያንግ በታህሳስ ወር 2022 የሳተላይቷ የመጨረሻ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን መግለጿን ሬውተርስ በዘገባው አውስቷል።
ሰሜን ኮሪያ በጠላት ላይ "ከፍተኛ ቀውስ" ያስከትላል ያለችውን ሚሳይል መሞከሯን አስታወቀች
በሙከራው ወቅት የተነሱ ናቸው የተባሉ የደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡልን ገጽታ የሚያሳዩ ምስሎችም ማውጣቷ አይዘነጋም።
ኪም ጆንግ ኡን በትናንቱ ጉብኝታቸውም በዚህ ወር መጨረሻ ትመጥቃለች ከተባለችው የስለላ ሳተላይት በተጨማሪ ሌሎች ለፒዮንግያንግ ወሳኝ መረጃዎችን የሚያቀብሉ መሳሪያዎች በብዛት እንዲሰሩ አሳስበዋል ነው ያለው ኬሲኤንኤ በዘገባው።
አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር የፈጠረችውን ወታደራዊ ትብብር አጥብቃ የምትቃወመው ሰሜን ኮሪያ፥ የሀገራቱን ስጋትነት ግምት ውስጥ ያስገባ ዝግጅት ማድረግ “ተፈጥሯዊ ግዴታ” ነው ብላለች።
የጃፓን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሂሮካዙ ማትሱኖ በበኩላቸው፥ ሰሜን ኮሪያ ሳተላይት አመጥቃለሁ ብትልም የትኛውም ከባለስቲክ ሚሳኤል ጋር የተያያዘ ሙከራ የመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀብን የሚተላለፍ ነው ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ የፈረንጆቹ 2023 አመት ከገባ ወዲህ 30 የሚደርሱ የሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች፤ የአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ወታደራዊ ልምምድ ካልቆመም እገፋበታለሁ ስትል ዝታለች።
ባለፈው አመት ታህሳስ ወር ላይም አምስት ድሮኖችን እስከ ሴኡል ድረስ በመላክ መሰለሏ የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናትን ሲያስወቅስ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በዚህ ወር መጨረሻ ትመጥቃለች የተባለችው የስለላ ሳተላይትም የጎርቤቷን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ፈጣን መረጃን እንደምታቀብላት ይታመናል።
ፒዮንግያንግ ሁለት የመሬት ቅኝት ሁለት ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ማምጠቋንም መረጃዎች ያሳያሉ።