የሰሜን ኮሪያ ልዩ ኃይል አባላት በሩሲያ ጉብኝት አደረጉ
ይህ ወታደራዊ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ትብብራቸውን የሚያጠናክር ወታራዊ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ የመጀመሪያው ነው
የጉብኝቱ አላማ እና ሩሲያ ውስጥ የትኛውን አካባቢ እንደሚጎበኙ አልታወቀም
የሰሜን ኮሪያ ልዩ ኃይል አባላት በሩሲያ ጉብኝት አደረጉ።
የሰሜን ኮሪያ ልዩ ሰልጣኝ አባላት ለጉብኝት ወደ ሩሲያ ማቅናታቸውን ሮይተርስ የሰሜን ኮሪያ ሚዲያዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ይህ ወታደራዊ ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ትብብራቸውን የሚያጠናክር ወታራዊ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
የሰሜን ኮሪያው ኬሲኤንኤ ቴሌቪዥን እንደዘገበው የኪም ሁለተኛ ወታደራዊ አካዳሚ ፕሬዝደንት ኪም ጁም ቾል የወታደራዊ ስልጠና ባለሙያዎችን በመምራት በትናንትናው እለት ወደ ሩሲያ አቅንተዋል።
የጉብኝቱ አላማ እና ሩሲያ ውስጥ የትኛውን አካባቢ እንደሚጎበኙ አልታወቀም።
በሀገሪቱ መስራች ስም የተሰየመው ይህ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ኃይል ማስልጠኛ ነው። የአሁኑ የሀገሪቱ መሪ ከም ጆንግ ኡን መሪ ለመሆን እየተዘጋጁ በነበረበት ወቅት ከስዊዘርላንድ ሲመለሱ ወታደራዊ ትምህርት የተከታተሉት በዚሁ ዩኒቨርስቲ ነው።
የወታደራዊ ዩኒቨርስቲው ልኡክ ጉብኝት፣ የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ሰኔ ወር ፒዮንግያንግን ከጎበኙ ወዲህ ወደ ሩሲያ የተደረገ የቅርብ ጊዜ ጉብኝት ሆኗል።
ፑቲን በፒዮንግያንግ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጋር "ኮምፕሬሄንሲቭ ስትራቴጂክ ፓርትነርሽፕ" የተሰኘ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚህ ስምምነት ሁለቱ ሀገራት፣ ከሁለቱ በአንደኛቸው ላይ ወታደራዊ ጥቃት ቢሰነዘርባቸው፣ አንዳቸው ሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ወታደራዊ ድጋፍ ወዲያውኑ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የሩሲያ እና ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሄደው ጦርነት የጦር መሣሪያ እያቀረበች ነው የሚሏት ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ግንኙት መጠናከር፣ ሴኡል እና አሜሪካን እንቅልፍ ነስቷቸዋል።
ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እያቀረበች ነው የሚለውን ክስ ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ነው ስትል በተደጋጋሚ አጣጥላዋለች።