ጽ/ቤቱ እንደገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጦርነቱ በኋላ የሱዳን ጦር መሪዎች ዋና መቀመጫ ወደሆነችው ፖርት ሱዳን ከተማ ገብተዋል
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ በዛሬው እለት ጠዋት ሱዳን መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በትዊተር ገጹ አስታወቋል።
ጽ/ቤቱ እንደገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጦርነቱ በኋላ የሱዳን ጦር መሪዎች ዋና መቀመጫ ወደሆነችው ፖርት ሱዳን ከተማ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ ለሱዳን ጦርነት ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ጥረታቸውን ይቀጥላሉ ብሏል ጽ/ቤቱ።
የሱዳን ጦርን በሚመሩት ጀነራል አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን በሚመሩት ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ መካከል ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር አጋማሽ የተጀመረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ኢትዮጵያ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ግጭቱን በንግግር እንዲፈቱ እንደምትፈልግ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ባወጣቻቸው መግለጫዎች መግለጿ ይታወሳል።
ግጭቱን በድርድር ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች እስካሁን አልተሳኩም።
በአሜሪካ እና በሳኡዲ አረቢያ አመቻችነት በጂዳ ተጀምሮ የነበረው ድርድር ያለውጤት መቋረጡ ይታወሳል።
በሱዳኑ ጦርነት ከ10 ሺ በላይ ስዎች የተገደሉ ሲሆን ከ2.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ተፋላሚ ኃይሎቹ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በማድረስ ክስ ቢቀርብባቸውም፣ እርስበርሳቸው ከመወነጃጀል ውጭ ኃላፊት አልወሰዱም።