የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች የደቡብ ኮሪያን የመከላከያ ኩባንያዎች ማጥቃታቸው ተነገረ
ፖሊስ ጥቃት የደረሰበት ኩባንያ የትኛው እንደሆነ እና የተወሰደው የመረጃ አይነት ምን እንደሆነ ግልጽ አላደረገም
ፖሊስ መንታፊዎቹን በአይፒ አድሬስ እና በተጠቀሙት ማሌዌር አማካኝነት መለየት ተችሏል ብሏል
የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች የደቡብ ኮሪያን የመከላከያ ኩባንያዎች ማጥቃታቸው ተነገረ።
የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊ ቡድኖች ለአንድ አመት ያህል አጠቃላይ ጥቃት በመክፈት የደቡብ ኮሪያን የመከላከያ ኩባንያዎች የውስጥ ኔትወርክ በመስበር መረጃ መስረቃቸውን የደቡብ ኮሪያ ፖሊስ በዛሬው እለት አስታውቋል
ዛሩስ እና ኪምሱኪ ተብለው የሚጠሩት እነዚህ የመረጃ መንታፊ ቡድኖች ከሰሜን ኮሪያ የደህንነት ቢሮ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እና በመከላከያ ኩባንያዎች ዳታ ሲስተም ውስጥ የተሳሳተ ኮድ ማገባታቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ፖሊስ ከብሔራዊ የደህንነት ቢሮ እና ከግል ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በመሆን መንታፊዎቹን በአይፒ አድሬስ እና በተጠቀሙት ማሌዌር አማካኝነት መለየት ችሏል።
በፈረንጆቹ 2022 በተጀመረው በዚህ ጥቃት፣ መንታፊዎች በኩባንያው ፐብሊክ ኔትዎርክ ውስጥ የተሳሳተ ኮድ በማስገባት የውስጥ ለውስጥ መረጃ ልውውጡ እንዲታወክ እና ሲስተሙን ከጥቃት የሚጠብቀው የሴኩሪቲ ፕሮግራም በጊዜያዊነት እንዳይሰራ አድርገዋል ብሏል ፖሊስ።
መንታፊዎች ለግል እና ለኦፊሴላዊ ኢሜል ተመሳሳይ የይለፍ ቃል የሚጠቀሙ የኩባንያው ሰራተኞች ያሳዩትን የደህንነት ክፍተት በመጠቀም የመከላከያ ኩባንያዎችን ኔትወርክ ሰብረው በመግባት ሚስጥራዊ መረጃ ወስደዋል።
ፖሊስ ጥቃት የደረሰበት ኩባንያ የትኛው እንደሆነ እና የተወሰደው የመረጃ አይነት ምን እንደሆነ ግልጽ አላደረገም።
ደቡብ ኮሪያ በዓለም ቀዳሚ ከሚባሉት የጦር መሳሪያ ላኪ ሆና ብቅ ብላለች። በቅርብ አመታት ውስጥ ሀገሪቱ ዋጋቸው በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ሜካናይዝድ ሀውቲዘር፣ ታንክ እና ተዋጊ ጀቶችን ለመሸጥ ስምምነቶች ተፈራርማለች።
የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊ ቡድኖች በደቡብ ኮሪያ የፋይናንስ ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት እና የመከላከያ ኩባንያዎች እንዲሁም በ2014 በኑክሌር ኃይል ኦፐሬተር ላይ ጥቃት አድርሰዋል።
ሰሜን ኮሪያ ግን ከጥቃቶቹ ጀርባ እጇ እንደሌለበት ታስተባብላለች።