የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች ሶስት ቢሊዮን ዶላር መዝረፋቸው ተገለጸ
አይነተ ብዙ ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎቿን በመጠቀም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ አግኝታለች ተብሏል
የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ዋነኛ ሀብት ማሰባሰቢያ መንገድ እንደሆነላትም የተመድ መርማሪ ሪፖርት አስታውቋል
የሰሜን ኮሪያ መረጃ መንታፊዎች ሶስት ቢሊዮን ዶላር መዝረፋቸው ተገለጸ፡፡
ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ ባደረገችው የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ምክንያት በመንግስታቱ ድርጅት እና ምዕራባዊያን ሀገራት ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ የመረጃ መንታፊዎችን በማሰማራት ገንዘብ መሰብሰቧ ተገልጿል፡፡
እንደ መንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ከሆነ 58 የመረጃ ምንተፋ ድርጊቶችን አድርጋለች የተባለ ሲሆን በአጠቃላይ 3 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ አግኝታለችም ተብሏል፡፡
እነዚህ የተደራጁ እና በሰሜን ኮሪያ መንግስት የሚደገፉት የመረጃ ጠላፊዎች ግዙፍ የምዕራባዊያን የንግድ ተቋማትን ኢላማ አድርገው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዳገኙ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሀገሪቱ ገንዘቡን በምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ አማካኝነት ገንዘቡን ወደ ሀገሯ ወስዳለችም ተብሏል፡፡
በዚህ አማካኝነት ያገኘችውን ገንዘብ የጀመረችውን ኑክሌር አረር የበለጠ በማስፋፋት ውጤታማ የኑክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቅ፣ የመረጃ እና ኮሙንኬሽን ሳተላይቶችን ማምጠቅ ጨምሮ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ማስወንጨፏም ተገልጿል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በአንድ ወር ውስጥ አምስተኛ ኢምባሲዋን ዘጋች
ሰሜን ኮሪያ ከሰሞኑ በቻይና የተሰሩ በሚል ስም የሰው ሰራሽ ጸጉር እና ተያያዥ የመዋቢያ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ስታቀርብ እንደቆየች መገለጹ ይታወሳል፡፡
ሀገሪቱ በተጠናቀቀው 2023 ዓመት ብቻ ከ1 ሺህ 600 ቶን በላይ ሰው ሰራሽ ጸጉር፣ ጺም እና ሌሎች የመዋቢያ ምርቶችን በመላክ 167 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘች ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ይህን ያልታሰበ ምርት ለምንግዜም ተቀናቃኟ ደቡብ ኮሪያ ሳይቀር በእጅ አዙር ስትሸጥ ነበር የተባለ ሲሆን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ጃፓን ዋነኛ የምርቶቿ መዳረሻ ሆነዋል ተብሏል፡፡
የሀገሪቱ ነጋዴዎች በሰሜን ኮሪያ የተመረቱ ሰው ሰራሽ ጸጉር ወደ ቻይና በማጓጓዝ በቻይና የተሰራ የሚል ስም እየጨመሩ ያለምንም እንከን ከፍተኛ ገቢ ሲያገኙ እንደቆዩ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡