የዩክሬን መንታፊዎች የሩሲያዊ መሰላቸውን መረጃ መጥለፋቸውን ገለጹ
ሩሲያ በ2016 የዴሞክራቶችን ሰነድ በመስረቅ ትራምፕ ወደ ስልጣን እንዲመጡ አድርጋለች የሚል ክስ ከዋሽንግተን ይደመጣል
የዩክሬን መረጃ መንታፊዎች በ2016ቱ ስርቆት ተሳትፎ አድርጓል በሚል የተከሰሰውን ግለሰብ መረጃ ነው መስረቃቸውን ያስታወቁት
የዩክሬን የመረጃ መንታፊዎች በ2016 የዴሞክራቶችን የምርጫ ቅስቀሳ ሰነድ በመስረቅ ከሩሲያ የመረጃ ጠላፊዎች ጋር ግንኙነት የነበረውን ግለሰብ ኢሜል መጥለፋቸውን ገልጸዋል።
“ሳይበር ሬዚስታንስ” የተሰኘው ቡድን ሰርጌ ሞርጋቼቭ የተባለውን ሩሲያዊ ኢሜል ሰብረው መግባታቸውን ነው ያስታወቁት።
ሞርጋቼቭ የሄላሪ ክሊንተንን ሚስጢራዊ መረጃ አጋልጦ ዶናልድ ትራምፕን ወደ ስልጣን ባመጣው የ2016ቱ ምርጫ በሩሲያ በኩል በመረጃ ምንተፋ ስራ ተሰማርቷል በሚል በ2018 በአሜሪካ ክስ የተመሰረተበት ግለሰብ ነው።
“ሳይበር ሬዚስታንስ” ሞርጋቼቭ የተላላካቸውን መልዕክቶችና አድራሻውን ይፋ አድርጓል።
ሬውተርስ የዩክሬን የመረጃ መንታፊዎች ያጋሩትን መረጃ ለማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል።
የዩክሬን መረጃ ጠላፊዎችን የቀደሙ እንቅስቃሴዎች የሚያጠኑት ስቴፋን ሶሳንቶ የተባሉ ባለሙያ ግን አሳማኝ መረጃዎች መሆናቸውንና የ2016ቱን የመረጃ ምንተፋ በጥልቀት ለማጥናት እንደሚያግዙ ነው የተናገሩት።
ሩሲያ በ2016 ዶናልድ ትራምፕን ወደ ስልጣን ለማምጣት የነበራትን ሚና የሚያረጋግጥ ነውም ባይ ናቸው።
ሩሲያም ሆነች የአሜሪካው የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ግን የዩክሬን የመረጃ መንታፊዎች ፈጸምነው ስላሉት ድርጊት ምላሽ መስጠት አልፈለጉም ይላል ሬውተርስ በዘገባው።
ሰርጌ ሞርጋቼቭ በአሁኑ ወቅት በሴንት ፒተርስበርግ በሚገኝ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ውስጥ እንደሚሰራ ዩክሬናውያኑ የመረጃ መንታፊዎች ገልጸዋል።
ኤፍ ቢ አይ ከዚህ ቀደም ባወጣው መረጃ ደግሞ ሞርጋቼቭ ጂ አር ዩ በተባለው የሩሲያ የስለላ ድርጅት ውስጥ ይሰራ እንደነበር ገመግለጹን ዘገባው ያወሳል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከባለፈው አመት የካቲት ወር ጀምሮ ጦርነት ውስጥ ከገቡ ወዲህ በሳይበር ጦርነቱም እየተፋለሙ ይገኛሉ።